Fana: At a Speed of Life!

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአፈፃፀም ተጠያቂነት ስርዓት ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራትን ለማምጣት የሚያግዝ የአፈፃፀም ተጠያቂነት ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የአስተዳደርና መሰረተልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር)÷ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ባሰፈረው ምክረሃሳብ፤ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ተቋማት በፋይናንስ አጠቃቀማቸው እንጂ በአፈፃፀም ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዓት እንዳልነበር አንስተው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተቋማት በአፈፃፀማቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መተግበር ይጀመራል ብለዋል።

በተጠያቂነት የአሰራር ስርዓት መሰረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቁልፍ ውጤት አመላካቾች ላይ ውል በማድረግ ስራቸውን እንደሚያከናውኑም ገልፀዋል።

የአፈፃፀም ተጠያቂነት ስርዓቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የተሻለ አፈጻጻም ያስመዘገቡት እውቅና እንዲያገኙ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ደግሞ የሚታረሙበት አግባብ የሚፈጠርበት መሆኑንም ነው ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ያስረዱት።

ሚኒስቴሩ በቀጣይም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ ያለውን ስብራት ማከም የሚችሉ የተለያዩ አሰራሮችን በጥናት እየለየ እንደሚተገብርም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.