Fana: At a Speed of Life!

በሚያዚያ ወር ከወጪ ንግድ ከ329 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 2 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2012 በጀት ዓመት በሚያዚያ ወር 329 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ገቢ መገኘቱንንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚህም ከግብርና ፣ ከማኑፋክቸሪንግ ፣ ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ እና ከሌሎች ምርቶች 365 ነጥብ1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈፃፀም የተከናወነው 329 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ከተገኘው 249 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ79 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በሚያዚያ ወር አገሪቷ ከግብርናው ዘርፍ 237 ነጥብ 47 ሚሊዮን ዶላር፣ ከማኑፋክቸሪንግ 23 ነጥብ 18 ሚሊዮን ዶላር፣ ከማዕድን ዘርፍ 64 ነጥብ 50 እና ከሌሎች ምርቶች 4 ነጥብ 14 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡

ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች ወርቅ፣ አበባ እና ቡና  መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የዕቅዱን ከ50 በመቶ እስከ 99 በመቶ  ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስጋ እና ጫት ናቸው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ለወሩ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ክንውን ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ቅመማ ቅመም፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቁም እንስሳት እና ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንደቅደም ተከተላቸው መሆናቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.