Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በሶስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ3ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ለከተማዋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ጉልህ ሚና ባላቸው ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት ተወያይቶ አጽድቋል።

በዚህም መሰረት:-

1ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የተሽከርካሪ አስተዳደር ህግ እና ሥርዓት ለማስከበር የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ ደንብን ለአሰራር በሚያመች መልኩ ሀሳብ ተሰጥቶበት ደንቡ ፀድቋል።

2ኛ. የከተማዋን ስታንዳርድ እና መዋቅራዊ ፕላን ለማስጠበቅ እንዲሁም መልሶ ማፍረስ እንዳይገጥም፤ ግንባታዎች ከመንገድ ያላቸው ርቀት ከዚህ በኋላ ወጥነት ያለው የከተማ አሰራር አንዲኖር በማሰብ ከመንገድ መራቅ ያለባቸውን 3 ደረጃዎች ለማውጣት በቀረበው መተዳደሪያ ደንብ ላይ በመወያየት፤ ከአሁን በኋላ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች ከዋና ከመንገድ በ10 ሜትር ርቀት መሆን እንደሚገባው፤ ከንዑስ ዋና መንገድ 5 ሜትር ርቀት፤ ሰብሳቢ መንገድ ደግሞ 3 ሜትር ርቀት በተጨማሪም የውስጥ ለውስጥ መንገድ 2 ሜትር ርቀት መጠበቅ እንዳለባቸው ካቢኔው ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

3ኛ. የነገዋ የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ ማዕከሉን በተለይም ለጎዳና ህይወት፤ ለፆታዊ ጥቃት ሰለባ እና ለወሲብ ንግድ ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች፣ መጠለያ፣ ማገገሚያ እና የተመሰቃቀለ ህይወታቸውን እንደገና ለማደስ የሚያስችል የሙያ እና ክህሎት ሥልጠናዎች የሚያገኙበትን እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያግዝ አቅም ያለዉ ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል በሚያግዘው ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ካቢኔው ተወያይቶ ማጽደቁን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.