Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ውዝፍ የጡረታ አበል ክፍያ ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ውዝፍ የጡረታ አበል ክፍያ መጀመሩ ተገለፀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከትግራይ ክልል ተወካዮች ጋር በነበራቸው ውይይት ከተሳታፊዎች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ውዝፍ የጡረታ ክፍያን በተመለከተ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄው ምላሽ እንደሚያገኝ ካረጋገጡ በኋላ ውሳኔ ተሰጥቶበታል።

በዚህም 65 ሺህ 873 ከሚሆኑት ውዝፍ የጡረታ አበል ተከፋዮች 90 በመቶ የሚሆኑት መረጃዎች ተጣርተው ከዛሬ ጀምሮ የ17 ወር ክፍያ እንዲፈጸም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ተለቋል ተብሏል።

መረጃዎች ተጣርተው በአጭር ጊዜ ይከፈላል ብለዋል የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳባ ኦሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፡፡

በዚህ መሰረት ከተጠቀሱት የዋና ባለመብቶች ትንሹ ውዝፍ ክፍያ 24 ሺህ 266 ሲሆን÷ ትልቁ ክፍያ 349 ሺህ 596 ብር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በክልሉ ካሉት አጠቃላይ የጡረታ አበል ተከፋይ 5 ሺህ የሚሆኑት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ወደ ጡረታ ስርአት የገቡ በመሆኑ ክፍያቸው ያልተቋረጠና አሁን እየተከፈላቸው ነው ተብሏል፡፡

ተተኪ የሚባሉ ወይም ወራሾች በ17 ወር ውስጥ እድሜያቸው ህጉ በሚጠይቀው መሰረት የስንት ወር ይደርሳቸዋል የሚለው እየተጣራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በፍርድ ቤት ሂደት ላይ የሚገኙና ውሳኔ ያገኙ በሚቀርቡ ማስረጃዎች መሰረት ክፍያው የሚፈጸም እንደሚሆንም ተመላክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ማንኛውም ጥያቄዎች በትግራይ ክልል አዲግራት፣ አክሱም፣ እንደስላሴ ፣ማይጨውና መቀሌ ቅርንጫፍን ጨምሮ በሀገሪቱ በሚገኙ ከ70 በላይ ቅርጫፎች ከቀረቡ ታይተው ምላሽ የሚያገኙበት ሁኔታም ተመቻችቷል ተብሏል፡፡

በኃይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.