Fana: At a Speed of Life!

የተለየ ክህሎት ያለው ሀይል መገንባቱ ግጭት ጠማቂዎችን ለመቆጣጠርና መረጃ ለመሰብሰብ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው – ም/ ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የተለየ ክህሎት ትጥቅና ብቃት ያለው ሀይል መገንባቱ ግጭት ጠማቂዎችን ለመቆጣጠርና መረጃ ለመሰብሰብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያሰለጠናቸውን የልዩ ኢንተለጀንስ ኦፕሬሽን ዩኒት አባላትን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን በዚህ ወቅት÷የተለየ ክህሎት ትጥቅና ብቃት ያለው ሀይል መገንባቱ ግጭት ጠማቂዎችን ለመቆጣጠርና መረጃ ለመሰብሰብ ጥልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው÷ ሰልጣኞቹ የተሸከሙት አደራ ምን እንደሆነና በቀጣይነት ራሳቸውን ማብቃት እንደሚገባቸው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

ሰልጣኞች በማንኛውም የአየር ሁኔታ ውስጥ ሆነው አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የተሰጣቸውን ተልዕኮ መወጣት የሚያስችላቸው ብቃትን የሚያላብስ አቅም ገንብተዋል ያሉት ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ቶላ ናቸው።

ሰልጣኞች ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችንና መሳሪያዎችን በመጠቀም ከተልዕኮ አካባቢዎች ጋር በመመሳሰል ጠላትን በማጥቃት መረጃ መንትፎ የማምጣት ብቃት መገንባታቸውን ፤ አስፈላጊ ከሆነም የደፈጣ ውጊያ የማድረግና ራሳቸውን የመከላከል ብቃት መገንባታቸውንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተጠረጠረ ሰው ወይም ተሽከርካሪን በመክበብ በቁጥጥር ስር በማዋልና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን የመውሰድ ስልቶችን በስልጠና ቆይታቸው ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በዚህም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንደሚወጡ በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል ብለዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.