Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ1 ነጥብ 72 ቢሊየን ዶላር የድጋፍና ብድር ስምምነት ተፈራረሙ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የ1 ነጥብ 72 ቢሊየን ዶላር የድጋፍ እና የብድር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የብድር እና የድጋፍ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚውሉ ስድስት ፕሮጀክቶችን ለመተገበር እንደሚውል ተገልጿል፡፡

የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመውታል፡፡

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 300 ሚሊየን ዶላር የሚሆነው በገጠር አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ማሳለጥ ለሚያስችል የመንገድ መሰረት ልማት ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል፡፡

200 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘውን የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ለማጠናከር እና ለማስፋፋት እንደሚውል የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ ከተሰጠው ብድር ውስጥ 340 ሚሊየን የሚሆነው በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር የማህበረሰብ ክፍሎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እንደሚውል ተጠቅሷል፡፡

522 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ለማስፋት እና ታዳሽ ሃይል ማመንጨት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመደገፍ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡

275 ሚሊየን ዶላር የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን እና ተደረሽነትን ለማስፋት እንዲሚውል ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.