Fana: At a Speed of Life!

የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም የሕብረተሰቡን ኑሮ የሚቀይሩ ተግባራት ማከናወን እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሃሰን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም የሕብረተሰቡን ኑሮ የሚቀይሩ ተግባራትን ማከናወን ይገባናል አሉ፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል የተከናወኑ የመንግሥት ሥራዎች አፈፃጸምን አስመልክቶ በየደረጃው በተደረጉ ውይይቶች ላይ የተነሱ ሐሳቦችን መሰረት ያደረገ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ተጠቅመን የሕብረተሰባችንን ኑሮ ከመሰረቱ የሚቀይሩ ተግባራት ማከናወን ይገባናል ብለዋል፡፡

ያለውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግም የአመራሩን በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠይቅ ማስገንዘባቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

ግብርናን በተመለከተም የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እና በየደረጃው ያለውን ባለሙያ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም በማዕድን ዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ክልላዊ ንቅናቄ እንደሚደረግ ጠቁመው ዘርፉን በልዩ ጥንቃቄ መምራት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ከሥራ ፈጠራ አንጻርም በሥራና ክኅሎት የሪፎርም ሥራ መሠራት እንዳለበት ገልጸው÷ ከሌሎች ባለድርሻ አካላትና ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር ሊኖር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

በመድረኩ ፈተናዎችን በመቋቋም በየዘርፉ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸው የተገለጸ ሲሆን÷ በቀጣይም የትምህርት ጥራት፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ሥርጭት፣ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ተከታትሎ መፍታት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.