Fana: At a Speed of Life!

በዶ/ር ሊያ ታደሰ የተመራ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመግታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጤና ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የተመራ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ቡድኑ የክልሉ ጤና ምርምር ኢንስቲትዩትና የኮቪድ 19 መመርመሪያ ላቦራቶሪ ማዕከልን የጎበኘ ሲሆን፥ የምርመራ ማዕከሉ አደረጃጀትና የባለሙያዎቹ ተነሳሽነት አበረታች መሆኑን መመልከታቸውን የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

ማዕከሉ በተለይ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ያገኘው ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ የክልሉ የጤና ቢሮ አመራሮች ገልጸዋል።

በመቀጠልም በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፅኑ ህሙማን ጨምሮ ለይቶ ለማከም የተዘጋጀውን ማዕከል ጎብኝተዋል::

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በጉብኝቱ ወቅት ከክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የመከሩ ስሆን፥ አመራሩ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለሆነ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰራ ላለው ስራ እስከሁን ከፌዴራል መንግስት እየተሰጠ ላለው የገንዘብ፣ የግብዐትና ሌሎች የቴክኒካል ድጋፍ የክልሉ አመራር ምስጋና አቅርቧል።

የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ እንዲሁም በክልሉ በተለይ በድንበር ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ ከስደት ተመላሾችና ስደተኞች እንዲሁም የአገር አቋራጭ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ እየታየ ያለውን ተጋላጭነት ታሳቢ በማድረግ የፌዴራሉ መንግስት በባለቤትነት ከክልሉ ጋር እንዲሰራና የሚደረገው ድጋፍ በቀጣይ እንዲጨምር ጠይቀዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ፥ የፌዴራል መንግስት አቅም በፈቀደ ሁሉ ለክልሎች፣ ለከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ላይ እየሰሩ ላሉ ተቋማት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል::

ዶክተር ሊያ አክለውም ከሚዲያ ባለሙያዎች ለክልል የሚደረገው የበጀትና የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ድጋፍ መስፈርት ምን እንደሆነ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፥  ለክልሎች የሚደረገው ማንኛውም ድጋፍ በዋነኛነት በፌዴሬሽን ቀመር መሆኑን ገልፀዋል።

በተወሰነ መልኩ ክልሎች በድንበር አከባቢ ለሚሰሩት ስራ፣ እንዲሁም ያለባቸውን የበሽታ ስርጭት ስጋት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.