Fana: At a Speed of Life!

44 ቢሊየን ዶላር ያጭበረበረችው ቬትናማዊት ቱጃር በሞት እንድትቀጣ ተወሰነ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 44 ቢሊየን ዶላር ያጭበረበረችው ቬትናማዊት ቢሊየነር በሞት እንድትቀጣ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ትሩኦንግ ማይ የተባለችው የ67 ዓመት ቬትናማዊት ቱጃር ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በሀገሪቱ ከሚገኘው ሳይጎን የንግድ ባንክ ለ11 ዓመታት ያህል ዘረፋ ስትፈፅም እንደነበር ተገልጿል፡፡

ግለሰቧ ከመዘበረችው ገንዘብ ውስጥ 27 ቢሊየን ያህል ዶላር ተመላሽ እንድታደርግ ብይን ቢሰጥም፤ ዐቃቤ ህግ ግለሰቧ ገንዘቡን መመለስ እንደማትችል በማረጋገጡ የሞት ቅጣቱ እንደተላለፈባት ተመላክቷል፡፡

ግለሰቧ የፈፀመችው ወንጀል ውስብስብ የወንጀል ድርጊት ሲሆን በአጠቃላይ 44 ቢሊዮን ዶላር ወይም 35 ቢሊዮን ዩሮ በመመዝበር የሞት ፍርድ የተፈረደባት የመጀምሪያዋ ቬትናማዊት ሆናለች ነው የተባለው፡፡

ቢሊየነሯ ትሩኦንግ ማይ በተለያዩ ሚስጢራዊ ኩባንያዎቿ የሸሸገችውን ሀብት በመጠቀም የወሰደችውን ገንዘብ የምትመልስ ከሆነ የሞት ፍርዱ ሊቀርላት እንደሚችል ተነግሯል።

በግለሰቧ የክስ ሂደቱ 10 አቃቤ ህጎች እና 200 ጠበቆች መሳተፋቸው የተገለፀ ሲሆን 2 ሺህ 700 ምስክሮች ቃላቸውን እንዲሰጡ የጥሪ ወረቀት እንደደረሳቸውና ከ5 ሺህ 400 ኪሎግራም በላይ የሚመዝኑ የሰነድ ማስረጃዎች በ104 ሳጥኖች መቅረባቸውም ተገልጿል።

በቬትናም ታይቶ አይታወቅም በተባለው ግዙፍ የፍርድ ሂደት ከቢሊየነሯ ጋር 85 ሰዎችም ክስ ቀርቦባቸዋል መባሉን የዘጋርዲያን እና ቢቢሲ ዘገባዎች አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.