Fana: At a Speed of Life!

ሦስት የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ አባል ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይጀሪያ ስቶክ ኤክስቼንጅን ጨምሮ ሦስት የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ አባል መሆናቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ሠነድ ሙዓለንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል እንደገለፁት÷ በመንግሥትና የግል አጋርነት መርህ የተመሰረተው ተቋሙ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ሰብስቧል።

ካፒታል የተሰባሰበው ከ16 ባንኮች፣ ከ12 ኢንሹራንሶችና ከ17 የፋይናንስ ዘርፍ ውጭ ከሆኑ ኩባንያዎች እንደሆነ ገልጸዋል።

የሠነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ የኢትዮጵያዊያን በአክሲዮን ገበያ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያሳድግ፣ የተራዘመ የፋይናንስ ዕድል የሚፈጥርና ለባንኮች ተጨማሪ ፋይናንስ ፍላጎት የሚጨመር እንደሆነም ገልጸዋል።

የግል 75 በመቶ ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ደግሞ 25 በመቶ ድርሻ ይዞ በተመሰረተው የሠነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ከሀገር በቀል ኩባንያዎች ባሻገር ሦስት የውጭ ድርጅቶች አባል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም የረዥም ጊዜ ልምድና ተሞክሮ ያለው የናይጀሪያ ስቶክ ኤክስቼንጅ ባለድርሻ መሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።

ፋይናንሻል ሴክተር ዲፕኒንግ አፍሪካ’ የተሰኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ የእንግሊዝ ድርጅትና በአፍሪካ ንግድ ገበያ ልምድ ያለው ‘የትሬድና ዴቨሎፕመንት ባንክ’ የካፒታል ድርሻ ባለቤት እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ተቋማቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው በተለያዩ ሠነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ አገልግሎት እንዲሳተፉ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ወደፊት የዕዳ ሰነዶችን መሸጥ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አመልክተዋል።

ዘመናዊና ደኅንነቱ የተጠበቀና የተቀላጠፈ የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ መመሥረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ገቢራዊ ለማድረግ የግዥና ሌሎች ሂደቶች መጠናቀቃቻውን እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.