Fana: At a Speed of Life!

በጽንፈኛው ኃይል አመራር እና አባል ላይ እርምጃ ተወስዷል- ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጽንፈኛው ኃይል አመራርና አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በተወሰደው እርምጃም÷ የፅንፈኛው አመራርና አንድ የቡድኑ አባል መገደላቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም አንደኛው በቁጥጥር ስር ውሏል ነው ያለው ፖሊስ፡፡

በዚህም ናሁሰናይ አንድአርጌ ታረቀኝ፣ አቤኔዜር ጋሻው አባተ እና ሀብታሙ አንድአርጌ ተሰማ የተባሉት የፅንፈኛው ቡድን አባላት በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ተልዕኮ ይዘው እየተንቃሰቀሱ መሆኑን የፀጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል እንደተደረሰበትም ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

የሽብር ተግባራቸውን ሳይፈፅሙ በቁጥጥር ስር ለማዋል የፖሊስ አባላት እንቅስቃሴ እያደረጉ ባለበት ሁኔታ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ ፅንፈኞቹ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህም በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2C 14373 አ/አ ሱዙኪ ዲዛዬር መኪናን በመጠቀም ከፖሊስ አባላት ጋር ተኩስ በመክፈታቸው ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ ቆስሎ ወደ ህክምና ከተላከ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ በተኩስ ልውውጡ መሃል መሞቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

እንዲሁም አቤኔዘር ጋሻው አባተ የተባለው የቡድኑ አባል ሳይቆስል በቁጥጥር ስር መዋሉን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

ፅንፈኞቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገ እንቅስቃሴ ሳጅን አራርሳ ተሾመ እና ኮንስታብል ማቲያስ ጴጥሮስ ሲቆስሉ አቶ እንዳሻው ጌትነት የተባሉ ግለሰብ ፅንፈኞቹ በመኪናቸው እንዲጭኗቸው ቢያስገድዷቸውም ግለሰቡ አልተባበር በማለታቸው በፅንፈኛው አባላት ተገድለዋል፡፡

አቶ እንደሻው ሲያሽከርክሯት የነበረቸው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2 አ/አ 80457 በጥይት ጉዳት እንደደረሰባት አዲስ አበባ ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በቀጣይ ፖሊስ የደረሰበትን ዝርዝር መረጃ እንደሚያስታውቅ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.