Fana: At a Speed of Life!

ክልከላ ተጥሎባቸው ከነበሩ ተሽከርካሪዎች መካከል 58ቱ ከጅቡቲ ወደ ድሬዳዋ ተጓጓዙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅቡቲ ወደብ ተከማችተው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ተጥሎባቸው ከነበሩ ተሽከርካሪዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ 58 መኪናዎች ተጓጉዘው ድሬዳዋ ወደብና ተርሚናል ደርሰዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ውሳኔ እስኪያገኙ ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲቆዩ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ነው ወደ ድሬዳዋ ወደብና ተርሚናል የተጓጓዙት፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ድሬዳዋ ወደብና ተርሚናል የተወሰዱት በአምስት መኪና ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሲሆን÷ በወደብና ተርሚናሉ በተዘጋጀላቸው ስፍራ ላይ እንዲሆኑ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ (ኢባትሎ) የድሬዳዋ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ማዘጋጀቱም ተጠቁሟል።

ቀሪ ተሽከርካሪዎች በቀጣይ ተጓጉዘው የሚገቡ ሲሆን÷ ኢባትሎ የተሰጠውን ሀገራዊ ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት ተግቶ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር ቀ/ሃ/7/14/525 ባስተላለፈው መመሪያ በውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ክልከላ ምክንያት ከመጋቢት 22 ቀን 2015 ዓ.ም በፊት የባንክ ፈቃድ የተሰጠባቸው ወይም ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ የተገዙ እና ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ያልቻሉ በጅቡቲ ወደብ ላይ ተከማችተው የሚገኙ ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ በኩል ተጓጉዘው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና በድሬደዋ ወደብና ተርሚናል ቆይተው ውሳኔ እንዲጠባበቁ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.