Fana: At a Speed of Life!

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በፅንፈኛው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በፅንፈኛው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአዲስ አበባ በህቡዕ በተደራጀው ፅንፈኛ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ÷ ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ የተባለው የፅንፈኛው ቡድን አመራር እና አቤነዘር ጋሻው አባተ የተባለ የቡድኑ አባል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ የተባለው የቡድኑ አባል ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተወጥኖ ለከሸፈው ህቡዕ የጥፋት ተልዕኮ ዋነኛ ጠንሳሽ የሆነው ናሁሰናይ አንዳርጌ የተባለው ግለሰብ የጽንፈኛ ቡድኑ መሪ እንደነበር የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫ አረጋግጧል።

ናሁሰናይ አንዳርጌ የጽንፈኛ ቡድኑ እኩይ ዓላማ እንዲሳካ የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ የመለመላቸው ወጣቶች ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የፋይናንስና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ከሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸው በማሰባሰብ ሁኔታዎችንም እንዳመቻቸ መግለጫው አትቷል፡፡

የፅንፈኛ ቡድን አባላት የተለያዩ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ህቡዕ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እይታ ውጭ አልነበሩም ብሏል መግለጫው።

የሸብር ቡድኑ አባላት በዛሬው ዕለት በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2C 14373 አ/አ ተሸከርካሪን በመጠቀም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ የሽብር ተግባራቸውን ለመፈፀም በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በፀጥታ ኃይሉ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፍቃደኛ ከመሆን ይልቅ በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ በመክፈት በሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት አደርሰዋል ብሏል መግለጫው።

በተጨማሪም አቶ እንዳሻው ጌትነት የተባሉ ግለሰብ የሽብር ቡድኑ አባላት በመኪናቸው እንዲጭኗቸው ቢያስገድዷቸውም አልተባበር በማለታቸው በፅንፈኛ ቡድኑ አባላት ተገድለዋል፡፡
ጽንፈኛ ቡድኑ በአማራ ክልል እያደረሰ ያለው ጥቃት እንደማያዋጣው በመረዳቱ ራሱን ወደ ሽብርተኝነት ቀይሮ በአዲስ አበባ እና አከባቢዋ የመጨረሻ መፍጨርጨር እያደረገ እንደሚገኝ የገለፀው የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል መግለጫ የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሰላም ወዳዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን እስከአሁን ድረስ እያደረገ ላለው ትብብር ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረበ ሆቴሎች፣ ገስት ሀውሶች፣ የቤት እና የመኪና አከራዮች እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.