Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ከጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ 14 አመራሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተከስቶ ከነበረው የጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ 14 አመራሮችና አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ኡሞድ ኡሞድ እንዳሉት ፥ በቁጥጥር ስር የዋሉት አመራሮች በጆር እና በኢታንግ ልዩ ወረዳ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ተሳትፈዋል የተባሉ ናቸው።

በተለይም በመጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም በጆር ወረዳ ለተከሰተው የሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም እጃቸው ያለባቸው 2 የዞን ከፍተኛ አመራሮችና 5 የወረዳ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በኢታንግ ልዩ ወረዳ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ለህግ እንዳይቀርቡ እንቅፋት የሆኑ 7 የወረዳ አመራሮች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ተገቢው ማጣራት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለያዩ መድረኮች በጋምቤላ ከተማ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት የሚሞክር አንድ ግለሰብ ከአመራሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉንም አስታውቀዋል።

በክልሉ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ ወደ ቀድሞ ሰላሙ እንዲመለስ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ መቅረቡንም የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.