Fana: At a Speed of Life!

እስራኤል ከኢራን የተወነጨፉባትን 300 ሰው አልባ አውሮፕላኖችና ሚሳኤሎች ማክሸፏን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በራሷና አጋሮቿ በኢራን ከተወነጨፉባት ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ውስጥ 99 በመቶውን ማክሸፍ መቻሏን አስታውቃለች።

ይሁንና በግዛቷ ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ድብደባ እንደተፈፀመና በዚህም በደቡባዊ እስራኤል የሚገኘው የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ካምፕ መመታቱን አንዲት ሕፃንም መቁሰሏን ገልፃለች።

ኢራን በእሥራኤል ላይ ጥቃት መሠንዘር መጀመሯን ተከትሎም መረጃዎች ተከታትለው በመውጣት ላይ ይገኛሉ።

እሥራኤል እየተሰነዘረባት ካለው ጥቃት የተነሳ አየር ክልሏን መሉ በሙሉ ዝግ ማድረጓ ተሰምቷል።

የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ላልተወሰነ ጊዜ የአየር ወሰናቸውን ዝግ ያደረጉ ሲሆን፤ ሶሪያ ፣ ኢራቅ ፣ ዮርዳኖስ እና ግብፅ የአየር ክልሎቻቸውን በጊዜያዊነት በመዝጋትም ከፍተኛ ተጠንቀቅ አውጀዋል።

ኢራን በእሥራኤል ላይ ከድሮንና የሚሳዔል ጥቃቶች በተጓዳኝ፤ የሳይበር ጥቃት መፈፀሟም ተነግሯል።

ከቴህራን የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት፤ በእሥራኤል የመከላከያ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሳይበር ጥቃት ተፈፅሟል።

ይሁንና ይህን የሳይበር ጥቃት ትክክለኝነት እስካሁን ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አለመቻሉ ተመላክቷል።

መዳረሻቸውን ወደ እሥራኤል ያደረጉ የኢራን ድሮኖች እንደ ግሪሣ ወፍ ምሽቱን በኢራቅ ሰማይ ላይ በብዛት የታዩ ሲሆን፤ ከዋክብት እንጂ ድሮኖች የማይመስሉበትን ምስል የኢራኑ ታዝኒም የዜና አውታር ይዞ ወጥቷል።

የአየር እና የባሕር ኃይል ምድብ ጣብያዎች እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ መኖሪያ የኢራን ጥቃት ዒላማ ተብለው ከተገመቱት መካከል እንደሚጠቀሱም ተመላክቷል።

ኢርና የዜና ምንጭ እንደዘገበው ከሆነ፤ ኢራን ወደ እሥራኤል ባላስቲክ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ ጀምራለች።

ከኢራን እየተሠነዘረ ባለው ጥቃት ቅድሚያ ተጠቂ ሊሆኑ ከሚችሉ አካባቢዎች ዜጎች እንዲርቁና ፡ ጥቃትን በሚቀንሱ መከለያዎች ውስጥ እንዲቆዩ ሲል የእሥራኤል መከላከያ ሠራዊት ለዜጎች ትዕዛዝ መስጠቱም ተነግሯል።

ለኢራን ጥቃት ተጋላጭ ናቸው ከተባሉት የእሥራኤል ይዞታዎችና ግዛቶች መካከል የጎላን ኮረብታዎች ፣ ኔቫቲም ፣ ዲሞና ፣ ኤይላትና በዙሪያቸው ያሉ ነዋሪዎች መሽገው እንዲቆዩ የእሥራኤል ጦር ለሀገሪቱ ዜጎች አሳስቧል።

ትናንት ምሽቱን ጥቃት የጀመረችው ኢራን ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችና ሚሳኤሎችን ወደ እሥራኤል አስወንጭፋለች።

ይሁንና ሰው አልባ አውሮፕላኖቹና ሚሳኤሎቹ የእሥራኤልን የአየር ክልል ከመጣሳቸው በፊት በእስራኤል በራሷና በአጋሮቿ በአሜሪካ፣ በብሪታንያ፣ በፈረንሳይ እና በዮርዳኖስ የአየር መከላከያ ኃይሎች እንዳከሸፏቸው አንድ የእሥራኤል መከላከያ ከፍተኛ ሹም ለ ዘ ታይምስ ኦቭ እሥራኤል ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.