Fana: At a Speed of Life!

ወደ 3 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ 250 ጤና ኬላዎችን ወደ ሁለተኛ ትውልድ አሳድገናል- ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ 3 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ 250 ጤና ኬላዎችን ወደ ሁለተኛ ትውልድ አሳድገናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሳ ገለፁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ በጤና ተቋማት አቅርቦትና ጥራት ላይ እየተሰራ ባለው ሰፊ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ መሻሻሎች እየታዩ ነው ብለዋል።

የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት፣ የሰው ሃይልና አስተዳደር፣ የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሳደግና ያሉትን በማደስ ለውጥ መገኘቱንም አንስተዋል።

“ይህ ለውጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ሀገርና ክልል ባጋጠሙን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች መካከል ተኩኖ የተገኘ ነው”ሲሉ ነው የገለፁት።

የቤተሰብ ብልፅግና እና የጤናማ ማህበረሰብ ግብ ስኬት፣ ሁለንተናዊ ለውጥ ድምር መሆኑን በመገንዘብ በጤናው ዘርፍ በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለንም ብለዋል።

ለአብነት “ኢማጂንግ ሴንተር” በተባለ ኢኒሼቲቭ 11 ክላስተር ስራ ለተደራጁ ሆስፒታሎች እንደ ሲቲ ስካን የመሳሰሉ ትልልቅ፣ ውድና ወሳኝ የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላት መቻሉን አንስተዋል፡፡

ወደ 3 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ 250 ጤና ኬላዎችን ወደ ሁለተኛ ትውልድ አሳድገናል፤በተጨማሪም የማያቋርጥ የመድኃኒት አቅርቦት ለማረጋገጥ በያዝነው አቅጣጫ የማህበረሰብ ሞዴል ፋርማሲዎችን 457 ማድረስ ችለናል ብለዋል፡፡

የህብረተሰብ ጤና መድህን አባላት ቁጥርን ወደ 27 ነጥብ 5 ሚሊየን አሳድገናልም ነው ያሉት።

በቀጣይም የማህበረሰቡን ጤና ለማረጋገጥ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.