Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በማስጠበቅ በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ሰፊ አበርክቶት ሲያደርጉ የቆዩት አምባሳደር አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) በሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች ከማገልገል በተጨማሪ የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል ።

አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) በሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች ከማገልገል በተጨማሪ የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል ።

አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) በኢኮኒሚክስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ከእስራኤል ሀገር፣ የሦስተኛ ድግሪያቸውን ከቡልጋሪያ ካርል ማርክስ ዩኒቨርስቲ ኦፈ ኤኮኖሚክስ እና ፖስት ዶክትሬታቸውን በእንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል። ከነዚህም በተጨማሪ በፖሊስነት ህይወታቸው የ9ኛ ኮርስ አባል የነበሩ ሲሆን በዘርፉ የኮለኔልነት ማዕረግ ላይ ደርሰዋል።

አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) በድህረ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በሶማሊያ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ሠላም እንዲሰፍንና የእስረኞች ልውውጥ እንዲደረግ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውተዋል። በቀጠናው የኢትዮጵያን ጂኦስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ የሚታወቁ ታላቅ የመረጃና ደኅንነት ባለሙያም ነበሩ።

የመረጃና ደኅንነት ሙያን በተመለከተ በእስራኤል እና በጀርመን የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመከታተልና ሙያው እውቀትን፣ ክህሎትን፣ አስተሳሰብንና ሥብዕናን መሰረተ አድርጎ አሻጋሪ ተቋም በሀገር ውስጥ እንዲገነባ በ 1974 ዓ. ም የስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል።

በአጼ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ስራ የሰሩት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ምንም ክስ ሳይቀርብባቸው ለ12 ዓመታት በእስር ቤት እንዲያሳልፉ የተደርጉ ሲሆን በእስር በቆዩባቸው አመታትም ሳይቀር በቆዩበት እስር ቤት ውስጥ የነበሩ ታራሚዎች የትምህርት እድል እንዲያገኙና ትምህርት እንዲስፋፋ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ከእስር ከወጡ በኋላም የዘመን ባንክን ጨምሮ በተለያዩ የግል ተቋማት አማካሪነትና ኃላፊነት አገልግለዋል።

አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ በኃላ በተደረገላቸው ተቋማዊ ጥሪ መሰረት የጤና መታወክ እስካጋጠማቸው ታህሳስ 2016 ዓ.ም ድረስ በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የነበሩ ሲሆን÷ በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ የደኅንነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሳል ትንታኔ በመስጠት ሀገራዊ ሀላፊነታቸዉን በታማኝነትና በቅንነት ተወጥተዋል።

አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) የሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የማስጠበቅ ስራ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ የእድሜልክና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆኑን በተግባር ያሳዩ ባለሙያ ነበሩ።

አስማማዉ ቀለሙ(ዶ/ር) ባደረባቸዉ ህመም በሀገር ዉስጥ እና በዉጭ ህክምና ሲደረግላቸው ቢቆዩም ቅዳሜ ሚያዝያ 05 ቀን 2016 ዓ.ም ለሊት ላይ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

የቀብር ስነ ስርዓታቸውም የፊታችን ማክሰኞ 9 ሰአት ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ እና የስራ ባልደረቦቻቸዉ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የሚፈፀም ይሆናል::

አስማማው ቀለሙ(ዶ/ር) ባለትዳርና የ ሦስት ወንዶች አባት ነበሩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.