Fana: At a Speed of Life!

ጄኔራል አበባው የጽንፈኛ ሃይሎችን አመራሮች የመመንጠሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑን ሸኔ እና የጽንፈኛውን ሃይል አከርካሪ በመስበር በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ ዞን አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል ሲሉ የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡

ጄኔራል አበባው ታደሰ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የሰሜን ሸዋ ዞን አሁናዊ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም በወደፊት የሥራ አቅጣጫ ላይ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ጋር ተወያይተዋል፡፡

ጄኔራል አበባው ፥ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አሸባሪውን ሸኔና ፅንፈኛ ኃይል አከርካሪውን በመስበር በሁለቱም ዞን አንፃራዊ ሰላም መስፈን መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

በከሚሴ ከተማ ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ከፍተኛ አመራሮችና ከሁለቱም ዞን ከተውጣጡ የአስተዳደር አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ፅንፈኛው ኃይል አዲስ አበባን ለማተራመስ ይመቸኛል ብሎ አለኝ ያለውን ኃይል በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ሰግስጎ ነበር ብለዋል።

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በወሰደው ፈጣን እርምጃም በሁለቱም ዞን የነበሩ ሁለቱን ጽንፈኞች በመምታት ሀገር የማተራመስ ቀቢፀ ተስፋቸውን በማምከን ውጤት ማስመዝገቡንም ነው ያነሱት፡፡

አሁን ለብቻው ተነጥሎና ተደብቆ የሚገኘውን የጽንፈኛ ኃይል አመራሮችን የመመንጠሩ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የኮማንዶና አየር ወለድ አዛዥ ሌ/ ጄ ሹማ አብደታ ፥ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔራሰብ እና ሰሜን ሸዋ ዞን የሀገሪቷን ሰላም በማናጋት የህዝቦቿን በሰላም የመኖር ዋስትናን ለማሳጣት ቆርጠው የተነሱትን ሁለቱንም ፅንፈኛ ኃይሎች በተገቢው መንገድ በመምታት የጥፋት ተልዕኳቸውን መክሸፉንም ነው የገለጹት።

ኮማንድ ፖስቱ ከኦፕሬሽናል ስራው ጎን ለጎን የአከባቢውን የፀጥታ ኃይል የማጠናከርና የማደራጀት ስራዎችን መስራቱን በማስታወስ ፥ አሁን በሁለቱም ዞን ለፀጥታው ኃይል ተግዳሮት የሚሆን ሃይል እንደሌለ ማረጋገጣቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.