Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ በሚል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ እያካሄደ ነው።
 
የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርጫን ከማራዘም ጋር በተያያዘ የቀረበለትን የህገ መንግስት ትርጓሜ ጥያቄ ከአተረጓጎም ፣ መርህ ፣ ዘዴና አላማ ይዘት ጋር ገምግሞ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፉን አስታውቋል።
 
በዚህም መሰረት
 
1. የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በሃገሪቱ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ ፣
 
2. ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የጤና ድርጅቶች ኮቪድ19ኝን በተመለከተ የሚያወጡትን መረጃ መሰረት በማድረግ የጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የሳይንሱ ማህበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የህዝብ ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡና ይህም በምክር ቤቱ ከፀደቀ ሃገራዊ ምርጫውን ከ9 ወር እስከ 1 አመት ማካሄድ እንደሚቻል የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።
 
ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማድመጥ እና በውሳኔው ላይ በመወያየት ኮሮና ቫይረስ ስርጭት በሃገሪቱ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ በሚል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቆታል።
 
የውሳኔ ሃሳቡ በአራት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ እና በ114 ድጋፍ በአብላጫ ድምጽ ነው የጸደቀው።
 
 
በተስፋዬ ከበደ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.