Fana: At a Speed of Life!

ተመድ ኢራንና እስራኤል ከግጭት እንዲታቀቡ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ኢራን እና እስራኤል ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ በሚል ስጋት እራሳቸውን እንዲቆጣጠሩ ጠይቋል፡፡

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ትናንት ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ ያለፉትን ሁለት ሳምንታት የአየር ድብደባ ተከትሎ ቀጣናውን ወደ ከፋ ውጥረት የሚከት ድርጊት እንዳይፈፀም አስጠንቅቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራቱ ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው ሌላውን የሰላም ጠንቅ በማለት እርስ በእርስ መወነጃጀል ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ነው እየተነገረ የሚገኘው፡፡

አሁን ጊዜው ግጭትን የማርገብ ነው ያሉት ጉቴሬዝ ፤ ቀጣናውም ሆነ ዓለም ተጨማሪ ጦርነት መሸከም አይችሉም ሲሉ ተናግረዋል።

በጋዛ ያለው ጦርነት በቀጣናው ባሉ የኢራን አጋሮች ሂዝቦላህ፣ ሃማስ፣ ሁቲ እና እስራኤል መካከል ግጭትን ቀስቅሷል ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን አንስተዋል፡፡

በፈረንጆቹ ሚያዚያ 1 ከፍተኛ ውጥረት ላነገሰውና በሶሪያ በሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት እስራኤል እስከ አሁን ኃላፊነት አለመውሰዷም ተመላክቷል፡፡

በተመድ የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ሮበርት ዉድ በበኩላቸው 15ቱ አባል ሀገራት በማያሻማ ሁኔታ ኢራን የፈጸመችውን ጥቃት እንዲያወግዙ ጠይቀዋል፡፡

አክለውም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የኢራን ድርጊት መልስ አልባ ሆኖ እንዳይቀር የማድረግ ግዴታ አለበት ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ ኢራንን ተጠያቂ ለማድረግ በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ እርምጃዎችን ትመረምራለች ማለታቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.