Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ምክትል ኮሚሽነር ዕጩ ጥቆማ መቀበል ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረተሰቡ ከዛሬ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ሰብዓዊ መብት ምክትል ኮሚሽነር እጩ መጠቆም እንደሚችል ተገለጸ።

ኮሚሽኑ የሴቶችና ሕፃናት ምክትል ኮሚሽነር ሥራ መልቀቃቸውን ተከትሎ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተወጣጡና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ስምንት አባላት ያሉት የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ ጀምራል።

ኮሚቴውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በሰብሳቢነት ሲመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ምክትል ሰብሳቢ ናቸው።

የኮሚቴው ጸኃፊ ባንቺይርጋ መለሰ በሰጡት መግለጫ÷ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ኮሚሽነር በፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ምትክ ለመሰየም የምልመላ መሥፈርትና የውስጥ አሠራር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በዚህም ኅብረተሰቡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ምክር ቤት በሚገኘው የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ፣ በኢሜል፣ በፖስታና በኦንላይን ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ገልጸዋል።

ለምክትል ኮሚሽነርነት ሚመረጡት ሴት እጩ ተወዳዳሪ ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶችንም እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከመሥፈርቶቹ መካከልም ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ተቆርቋሪ የሆነች፣ በሕግ ሙያ ሰፊ ልምድና ዕውቀት ያላት፣ በሥነ-ምግባርና በሥራ ታታሪነት የተመሰገነች እንዲሁም የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነች የሚሉት ይገኙበታል።

ኮሚቴው ከጥቆማ በኋላ ዕጩዎችን በመሥፈርቱ መሰረት የመለየትና የማጣራት ሥራ በመሥራት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለምክር ቤቱ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.