Fana: At a Speed of Life!

የትራንስፖርት ስምሪትና የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የስምሪት ሃላፊዎችና የትራንስፖርት ማህበራት አመራሮች ዋስትና እንዲታገድ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርት ስምሪት እና የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የስምሪት ሃላፊዎችና የትራንስፖርት ማህበራት አመራሮች ዋስትና እንዲታገድ ተጠየቀ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዛሬ ቀጠሮው በአዲስ አበባ መናኸሪያዎች የሚገኙ የመንገድ ትራንስፖርት ቅርጫፍ የስምሪት ሃላፊዎች፣ የትራንስፖርት ማህበራት አመራሮችና በነዳጅ ድጎማ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ደላሎችን ጉዳይ ተመልክቷል።

ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት ተቋም ጋር በጋራ በመሆን ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ የምርመራ ስራ እያከናወነ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ የሰራውን የምርመራ ማጣሪያ ስራና እና ቀሪ ምርመራዎችን በዝርዝር አቅርቦ ከጠበቆች ጋር ክርክር ተደርጓል።

ተጠርጣሪዎቹ የቀድሞ የህዝብ ትራንስፖርት የተሽከርካሪ ዘርፍ ሃላፊ እና የትራንስፖር ሎጂስቲክ ሚኒስትር አማካሪ የነበሩት ከድል ማግስት ኢብራሂም በከር፣ የትራንስፖርት ማህበራት አመራርና አባል ታምራት በየነ፣ ጌትነት በየነ እንዲሁም የመናኸሪያ የትራንስፖርት ስምሪት ሃላፊዎች አበበ ወ/መስቀል፣ ሺመት መሸሻ፣ ታምራት ለገሰ፣ ጥበቡ ተፈሪ ፣ እንግዳ ሽኩር፣ ባርናባስ አለሙ፣ ሙስጠፋ ጀማል እና ይታገሱ ተድላ ይገኙበታል።

መንግስት ህዝብን በትራንስፖርት አገልግሎት ለመደገፍ ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ማህበራትን የነዳጅ ድጎማ እንዲያገኙና አገልግሎቱን እንዲሰጡ ለማስቻል ባዘጋጀው የድጎማ መርሐ ግብር ላይ በጥቅም በመመሳጠር የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር ፣ለግል ጥቅም በማዋል መንግስት ላይ ከ34 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈጽምና ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ መሆናቸውን ጠቅሶ÷ፖሊስ የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ አቅርቧል።

በተጨማሪም ፖሊስ ከአንድ በላይ ተሽከርካሪ ያላቸው ባለንብረቶች በሙሉ የመስመር ስምሪትን ለራሳቸው በመያዝ ፣ ለሁሉም ማህበሮች ኮንትራት እንዲሰጥ ጨረታ ሲወጣ ጨረታውን በማጭበርበር ለራሳቸው በመውሰድ፣ ለስምሪትና ለመንገድ ትራንስፖርት ሃላፊዎች ጉቦ በመስጠት፣ የስምሪት ቦታ ሳይወጡ ለህዝብ አገልግሎት ሳይሰጡ የነዳጅ ድጎማውን ወስደው የራሳቸውን የኮንትራት ስራ መስራት፣ ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጡ የክፍያ ተጠቃሚ መሆን፣ በተበላሹ በቆሙ ተሽከርካሪዎችና በሀሰተኛ ታርጋ ቁጥሮች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ መሆንና፣ ከነዳጅ ማድያዎች ጋር በመመሳጠር በሊትር ኮሚሽን በመያዝ በድጎማ የሚቀዱትን ነዳጅ በጥቁር ገበያ መሸጥና በመንግስት ላይ ጉዳት ማድረስ የሚሉ ነጥቦችን ጠቅሶ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በዝርዝር አቅርቧል።

በዚህ መልኩ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ውስጥ የ11 የተጠርጣሪዎችን ቃልና እና የ9 ሰዎች ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ፣ የቴክኒክ ማስረጃዎች እንዲሰጡት የሚመለከተውን ተቋም መጠየቁን ገልጿል።

ቀረኝ ያላቸውን ማለትም ቀሪ ምስክሮችን የመቀበልና ከተቋማት ማስረጃዎችና የኦዲት ሪፖርት የማቅረብ ስራ እንደሚቀረው ጠቅሶ÷በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59/2 መሰረት የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በኩል በፖሊስ የተጠቀሰውን የጊዜ መጠየቂያ ምክንያቶች ተጨማሪ ጊዜ ለማሰጠት አሳማኝ አይደሉም በማለት ተከራክረዋል።

ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ኦዲት ሪፖርት ለማቅረብ እና የ30 ሰው ምስክር ቃል ለመቀበል በሚል በተመሳሳይ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁን አስታውሰው÷ በድጋሚ መጠየቁ ተገቢ አይደለም በማለት የመከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

ማን ምን አደረገ የሚለው የተጠርጣሪዎች ተሳትፎ በኦዲት ሪፖርት ተለይቶ ባልቀረበበት ሁኔታ ላይ ግለሰቦቹ በስር ሆኖ ሊቆዩ አይገባም በማለት የደንበኞቻቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል።

ፖሊስ በበኩሉ በጠበቆች ለተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦች ላይ መልስ የሰጠ ሲሆን ፣በዚህም ተጠርጣሪዎቹ በስር ላይ ሆነው ምስክሮች ላይ በመናኸሪያ ውስጥ በሚሰሩ ግለሰቦች በኩል ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን አመልክቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ምስክር ሊያስፈራሩ እና ካላቸው ደረጃ አንጻር ማስረጃ ሊያጠፉበት እንደሚችሉ ስጋቱን በመጥቀስ ዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም መልስ ሰጥቷል።

መዝገቡን በተመለከቱት የችሎቱ ዳኛ በኩል ምስክርን በሚመለከት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈለገበት ምክንያትን ፖሊስ እንዲያብራራ በቀረበ ጥያቄ መሰረት ፖሊስ ቀሪ ምስክሮች ከአዲስ አበባ ውጪም የሚገኙ መኖራቸውን ጠቅሶ÷ በብሔራዊ መረጃ ደህንነት በኩል የሚመጡ ምስክሮች ቃል እንደሚቀበልና ቀሪ ምስክሮችን ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገውና ምስክሮች በፍጥነት እንዲመጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጾ መልስ ሰጥቷል።

” የሚሰበሰቡ ማስረጃዎችን በሚመለከት ግለሰቦቹ ማስረጃ የማጥፋት አቅም አላቸው ወይ ? “ተብሎ በዳኛ በኩል ለቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጠው ፖሊስ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች እንደመሆናቸው ከመስሪያ ቤታቸው የሚመጡ ማስረጃዎችን ሊያጠፉ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ገልጿል።

ተሳትፏቸው አልተጠቀሰም ለሚለው የጠበቃ መቃወሚያን በሚመለከት ከመንገድ ትራንስፖርት የሚመጣ ወርኃዊ ስምሪት መሰረት መስመርተኛ እያለ የሚፈልጉትን የመስመር ስምሪት ለሚፈልጉት ሰው በመስጠትና በጥቅም በመመሳጠር እረገድ ማን ምን ተሳትፎ አለው የሚለውን ለማሳያ የእያንዳንዱን ተሳትፎ ማቅረቡን ጠቅሶ÷ ተሳትፏቸውን በኦዲት ሪፖርት ለማረጋገጥ ማረጋገጫ እንዲመጣ መጠየቁን አንስቷል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ፖሊስ ቀረኝ ካላቸው ስራዎች አንጻር ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ማስረጃ ሊያጠፉ የሚችሉበት እድል ሊኖር አይችልም የሚለውን ግምት በመያዝ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መፍቀድ ተገቢነት የለውም በማለት ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የ50 ሺህ ብር ዋስ አሲዘው ከስር እንዲፈቱ የፈቀደ ቢሆንም ፖሊስ በመዝገቡ ላይ ይግባኝ ብሏል።

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ የይግባኝ ማመልከቻውን እስከ ፊታችን ረቡዕ እስኪያቀርብ ዋስትናው መታገዱን ገልጿል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.