Fana: At a Speed of Life!

ዴንማርክ በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዴንማርክ የልማት ፖሊሲ ምክር ቤት በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዴንማርክ የልማት ፖሊሲ ምክር ቤት ሊቀመንበር አን ሜት ኪጀር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ዴንማርክ በግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ድጋፍና አጋርነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ዙሪያ መክረዋል፡፡

ዘርፉን ወደተሻለ ምርታማነት ለማሸጋገር በሚደረገው ርብርብ ዴንማርክ እስካሁን እያደረገች ላለው ድጋፍ ሚኒስትሩ አመስግነዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ዘርፍ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስና ለማስተካከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ጠቅሰው÷ ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወነ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ 32 ነጥብ 78 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የመስኖ ስንዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮች እያስመዘገቡ ያለው ውጤት የግብርናውን ዘርፍ በእጅጉ እያሳደገው ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ በግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የአረንጓዴ ልማትና በሌሎችም ሥራዎች እየተሠሩ ያሉ ተሞክሮዎችን አብራርተዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ የግብርናውንና የምግብ ሥርዓት ሽግግር እውን ለማድረግ መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልጸው÷ የዘርፉን ልማት ለመደገፍ ዴንማርክ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑም በግብርናው ዘርፍ በተለይም በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ በግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተርና በአረንጓዴ ልማት እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግኖ÷ በቀጣይም አብሮ ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.