Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ማክሮን ለጋሾች ለሱዳን 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለአንድ ዓመት በዘለቀውና ህዝቡን የረሃብ አፋፍ ላይ በጣለው ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ሱዳን የዓለም ለጋሾች ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በፓሪስ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ መጨረሻ ላይ ንግግር ያደረጉት ማክሮን ለሱዳን 51 ሚሊየን ህዝብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥሪ ማስተላለፋቸው ተነግሯል።

ድጋፉም ለምግብ፣ ለውሃ፣ ለመድሃኒት እና ለሌሎች አስቸኳይ ፍላጎቶች እንደሚውልም ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በንግግራቸው ሁላችንም የተገኘንበት ይህ ቅስቀሳ ለተፋላሚዎች ግልፅ መልእክት ያስተላልፋል ብለዋል።

ለንፁሃን ጥበቃ ሲባልም፤ ለዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የከበረ ጥሪ እናቀርባለን ሲሉ መናገራቸውንም አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

በጉባኤው የታደሙት ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሀላፊዎችና የእርዳታ ኤጀንሲዎች የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲከላከሉ፣ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እና ለሰላም አፋጣኝ ዓለም አቀፍ የሽምግልና ጥረቶች እንዲደረጉ ጠይቀዋል።

የሱዳን ሲቪል ማህበረሰብ አባላት በፓሪስ ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፤ ነገር ግን የሱዳን ጦርም ሆነ ተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ወታደራዊ ኃይል አለመወከላቸው ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.