Fana: At a Speed of Life!

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እየተባባሰ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እየተባባሰና ጥፋትም እያስከተለ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ያለበትን ሁኔታ የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

የሪፖርቱ መረጃዎቹ በሁለት መንገድ መሰባሰቡ የተገለጸ ሲሆን÷ የመጀመሪያው ከፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ዩ-ቲዩብ እና ኤክስ በናሙና መረጃዎች መሰብሰባቸው ተገልጿል።

ሁለተኛው የሕዝብ አስተያየት ማካተት በማስፈለጉ በአምስት ክልሎች በመጠይቆች እና በነፃ የስልክ መስመር መረጃዎች መሰብሰባቸው ታውቋል።

የባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ ኤደን አማረ በሰጡት ማብራሪያ÷ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ መስፋፋት በተለይም በግለሰቦችና በኅብረተሰብ ደኅንነት ላይ አደጋ ደቅኗል ብለዋል፡፡

ከጥላቻ ንግግር ምንጮች መካከልም በዋናነት አንዳንድ የሐይማኖት አባቶች፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የማኅበራዊ ይዘት አመንጪዎችና ግለሰቦች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በስድስት ወራት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት የጭካኔ አገላለጽ የሚስተዋልበት የመረጃ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበትና በተለይም በቴሌግራም 65 በመቶ የሥርጭት ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

የጥላቻ ንግግሩ ዒላማዎች ያነጣጠሩት በብሔር፣ ሐይማኖት፣ ቋንቋ እና ሌሎች የወል ማንነቶች፣ በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞችና በባለሥልጣናት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሐሰት አውድ እና የተሳሳተ መረጃ እንዲሁም በፈጠራ የተቀነባበረ ይዘት ያለው መረጃዎች በብዛት የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ የሚሰራጭባቸው መንገዶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ቀደም ሲል የብሔር ተኮር ማንነቶች ላይ በስፋት ያነጣጠረ እንደነበር አስታውሰው÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል ብለዋል።

በቅንብር የጭካኔ ድርጊቶችን በማጉላት ስጋትና ጥርጣሬ እንዲያይል የማድረግ ሁኔታዎች በስፋት መንፀባረቃቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ከፍተኛ ችግር እየሆነ በመምጣቱ የመከላከልና መግታት ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎች ባወጡት አሠራር መሠረት ደንብና መመሪያዎችን አክብረው ግዴታና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.