Fana: At a Speed of Life!

እስራኤል በኢራን የሚሳኤል መርሀ ግብር ላይ አዲስ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን ያልተጠበቀ ጥቃት በግዛቷ ላይ ማድረሷን ተከትሎ እስራኤል በኢራን የሚሳኤል መርሀ ግብር ላይ አዲስ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ እያቀረበች ነው።

እስራኤል በኢራን ላይ ምን ዓይነት የአፀፋ እርምጃ ትወስዳለች በሚል ብዙዎች በመጠባበቅ ላይ ቢሆኑም፤ እስራኤል ግን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ ለመስጠት እየሞከረች መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በጋዛ ያለው ትኩረት መደብዘዙን ተከትሎ እስራኤል በመጠኑ የተገለለች እንዳስመሰላትና ይህንንም አጋጣሚ በኢራን ላይ ዓለም አቀፍ ጫና ለማሳደር እንደምትጠቀምበት ተስፋ ማድረጓ ተገልጿል፡፡

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ለ32 ሀገራት ደብዳቤ መፃፉ ተነግሯል።

ይህም በኢራን የሚሳኤል መርሀ ግብር ላይ የሚጣለውን ማዕቀብ እንደሚጨምርም ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በኢራን የሚሳኤል መርሀ ግብር ላይ የጣለው ተከታታይ ማዕቀብ ባለፈው በፈረንጆቹ ጥቅምት ወር ጊዜው ማብቃቱ ተነግሯል፡፡

ይሁን እንጂ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሀገራት ባሉት ላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን መጣላቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢራንን እያስተዳደረ ያለው እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ኮርፖሬሽን አሸባሪ ድርጅት ተብሎ እንዲፈረጅም ጥሪ ማቅረቡን ቢቢሲ ዘግቧል።

አሜሪካ ቀድሞውንም አስተዳደሩን በአሸባሪነት እንደፈረጀችው የሚገልፀው ዘገባው፤ ብሪታኒያ ግን አለመፈረጇን አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.