Fana: At a Speed of Life!

በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ስርዓተ ቀብር በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ።

ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ ለ60 ዓመታት ያህል በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ያገለገሉት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ባደረባቸው ህመም በሀገር ውስጥና በውጭ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል።

በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከማገልገል በተጨማሪ የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆንም ያገለገሉት አስማማው (ዶ/ር)፤ ዘመን ባንክን ጨምሮ በተለያዩ የግል ተቋማት በአማካሪነት እና በኃላፊነት አገልግለዋል።

በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእስራኤል ሀገር፣ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከቡልጋሪያ ካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢኮኖሚክስ እንዲሁም ፖስት ዶክትሬታቸውን እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል።

ከእነዚህም በተጨማሪ በፖሊስነት ህይወታቸው የ9ኛ ኮርስ አባል የነበሩ ሲሆን የኮሎኔልነት ማዕረግ ላይ ደርሰዋል።

በድህረ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በሶማሊያ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ሠላም እንዲሰፍን እና የእስረኞች ልውውጥ እንዲደረግ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በቀጣናው የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ጥቅም በማስጠበቅም የሚታወቁ ታላቅ የመረጃና ደኅንነት ባለሙያ ነበሩ።

የመረጃና ደኅንነት ሙያን በተመለከተ በእስራኤልና በጀርመን የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመከታተልና ሙያዊ እውቀትን፣ ክህሎትን፣ አስተሳሰብንና ስብዕናን መሰረት አድርጎ አሻጋሪ ተቋም በሀገር ውስጥ እንዲገነባ በ1974 ዓ.ም የስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል።

አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ በኋላ በተደረገላቸው ተቋማዊ ጥሪ መሰረት የጤና መታወክ እስካጋጠማቸው ታህሳስ 2016 ዓ.ም ድረስ በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የነበሩ ሲሆን በዛሬው እለት ስርዓተ ቀብር በቅድስት ስላሴ ካቴድራል መፈጸሙን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዶክተር አስማማው ቀለሙ ባለትዳር እና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.