Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 108 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 108 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አደም ኑሪ እንደገለጹት÷ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 109 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 108 ቢሊየን ብር ሰብስቧል፡፡

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ45 በመቶ እድገት ወይም የ34 ቢሊየን ብር ጭማሪ ማሳየቱንም ጠቅሰዋል።

ቢሮው ገቢውን የሰበሰበው ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክስ አገልግሎቶች ገቢ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ እና ሌሎችም መሆኑን አስረድተዋል።

ቢሮው በሀሰተኛ ደረሰኝ የሚፈፀም ግብይትን ለመቆጣጠር ባደረገው ክትትል ከ5 ሺህ በላይ ግብይቶች በሀሰተኛ ደረሰኝ መፈጸማቸውን ማረጋገጡንም አስታውሰዋል፡፡

በሀሰተኛ ደረሰኝ ግብይት ሲፈፅሙ ከተገኙ ግብር ከፋዮች ላይም በአጠቃላይ 225 ሚሊየን ብር የገንዘብ ቅጣት በማስከፈል አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በበጀት ዓመቱ ከ140 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም ስኬት ሁሉም በየደረጃው ርብርብ እንዲያደርግና ግብር ከፋዩም በታማኝነት ግብሩን እንዲከፍል አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.