Fana: At a Speed of Life!

የ2 ዓመት ሕጻንን በመጥለፍ ወደ ሱሉልታ ከተማ በመውሰድ ደብቃ የተያዘችው ግለሰብ ጥፋተኛ ተባለች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁለት ዓመት ሕጻንን በመጥለፍ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ በመውሰድ ደብቃ ተይዛለች የተባለችው ተከሳሽ ጥፋተኛ ተባለች።

በቤት ሰራተኛነት በምትሰራበት ቤት ውስጥ ሶሊያና ዳንኤል የተባለች ሕጻንን ደብቃ በተያዘችው ተከሳሽ ላይ በሰባት ተደራራቢ ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ነው።

በተጨማሪም ችሎቱ ከተከሳሿ ጋር የተሰረቀ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር በመግዛት በመሸሸግ ወንጀል የተከሰሰውን ሌላኛውን ተከሳሽም ጥፋተኛ ብሎታል።

የፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ እንደተመላከተው÷ተከሳሽ ቤዛዊት በቀለ ለጊዜው ካልተያዙ ገብረአበሮቿ ጋር በመሆን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ክ/ከ ወረዳ 9 ሳሪስ አዲስ ሰፈር አካባቢ ተቀጥራ ከምትሰራበት መኖሪያ ቤት ሕጻን ሶሊያናን ጠልፋ ወደ ሱሉልታ ከተማ መውሰዷ በክሱ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስና የፌደራል ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባደረጉት ክትትል በሱሉልታ ከተማ ለዚሁ ወንጀል መጠቀሚያ በተዘጋጀ ባዶ ቤት ውስጥ ሕጻኗን ይዛ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋሏን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።

በዚህም የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 590 ንዑስ ቁጥር 1 ለ እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፋለች ተብላ በዋና ወንጀል አድራጊነት ለአካለ መጠን ያልደረሰች ሕጻንን መጥለፍ ወንጀል ተከሳ ነበር።

በ2ኛው ክስ ተከሳሿ ከመኖሪያ ቤቱ የሞባይል ስልኮችንና 2 ግራም ሀብል ወርቅን ጨምሮ 32 ሺህ 100 ብር የሚገመት ንብረትን ሰርቃ መሰወሯን በመጥቀስ ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ህግ አንቀጽ 669 ንዑስ ቁጥር 2 (መ) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፋለች በማለት በከባድ የስርቆት ወንጀል ክስ አቅርቦባታል።

እንዲሁም ተከሳሿ ህጻን ሰርቃ በቁጥጥር ስር መዋሏ በመገናኛ ብዙኃን መረጃው ከተሰራጨ በኋላ የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ስትሰራባቸው ከነበሩ መኖሪያ ቤቶች ላፖቶፕ ኮምፒዩተርን ጨምሮ ንብረት ተሰርቆብናል ያሉ ግለሰቦች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ማጣሪያ ተደርጎ በ5 ከባድ የስርቆት ወንጀል ክስ ተመስርቶባት ነበር።

ሁለተኛ ተከሳሽ ሀ/ኢየሱስ ኮርጃን በሚመለከት አንቀጽ 669 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ አንደኛ ተከሳሽ ከሌላ የግል ተበዳይ የሰረቀችውን ላፕቶፕና ኮንፒዩተርን የተሰረቀ ንብረት መሆኑን እያወቀ በ16 ሺህ ብር ከ1ኛ ተከሳሽ በመግዛት መሸሸግ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተባቸው ክስ በችሎት በንባብ ከተሰማ እና የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ከመዘገበ በኋላ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ተሰምቷል።

አንደኛ ተከሳሽ በቀረበባት ተደራራቢ ክሶች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተቆጠሩ 30 ምስክሮችንና በኢግዚቪት የተያዙ ማስረጃዎች እንዲሁም ገላጭ ተንቀሳቃሽና የፎቶ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም በተከሳሾች ላይ የቀረቡ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ በተከሰሰችበት ተደራራቢ ሰባት የክስ ድንጋጌ አንድትከላከል ብይን ተሰጥቷል።

ሁለተኛ ተከሳሽ በቀረበበት አንድ ክስ ላይ የተሰሙ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃን ለመጠባበቅ ከአራት በላይ ቀጠሮዎች የተሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ መከላከያ ማስረጃ ያላቀረቡ ሲሆን በተለይ አንደኛ ተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ ማቅረብ እንደማትችል ለችሎቱ ገልጻለች።

ፍርድ ቤቱም አንደኛ ተከሳሽን በተከሰሰችባቸው ተደራራቢ ክሶች ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሟ መረጋገጡ ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባታል።

ሁለተኛ ተከሳሽን በሚመለከት ማስረጃ በተሰማበት በአንድ ክስ ብቻ ጥፋተኛ ተብሏል።

አንደኛ ተከሳሽ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ከአዲስ አበባ ውጪ እንደምታመጣ ጠቅሳ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣት ጠይቃለች።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅና ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.