Fana: At a Speed of Life!

ከባድ የማታለል ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ሲፈለግ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ አስተዳደር በከባድ የማታለል ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ሲፈለግ የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ግለሰቡ በሸገር ከተማ አስተዳደር በመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ አራት ሀሰተኛ ስሞችን በመጠቀም በ15 ግለሰቦች ላይ ከባድ የማታለል ወንጀሎች በመፈፀም ተጠርጥሮ ክስ ተመስርቶበት ሲፈለግ መቆየቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግኝኙነትና ኮሚንኬሽን ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠርጣሪውን በተገኘበት እንዲያዝ ከፍርድ ቤት መያዣ ጋር በመላካቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መረጃ ኢንተለጀንስ እና የወንጀል ምርመራ ክትትል አባላት አሰማርቶ ግለሰቡን በመከታተል በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ አስተዳደር 02 ቀበሌ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አመልክቷል፡፡

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ሲውል የቤት ፕላን፣ የተለያዩ የባንክ ደብተሮች፣ አንድ ላፕቶፕ፣ የመኪና ቁልፍ እና የእጅ ስልክ መያዙን የገለጸው ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዉን ለሸገር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስረክቧል፡፡

በክትትል ሂደቱ መረጃ እና ጥቆማ በመስጠት ድጋፍ ላደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የፖሊስ አባላት ምስጋና በማቅረብ፤ ወንጀልን በጋራ መከላከል የሁሉም ኃላፊነትና ግዴታ በመሆኑ ህዝቡ ከፖሊስ ጎን እንዲቆም ኮሚሽኑ ጥሪ ማቅረቡን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

ወንጀልን ለመከላከል ሁለቱ ክልሎች በጋራ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.