Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች ቀጥለው ቀርበዋል፡-

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የፌዴራል መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን ረቂቁ በ29ኛው የሚኒስትሮች ም/ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ የፀደቀውን የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ፖሊሲውን ለማስፈፀም እንዲቻል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ በ2010 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው አዋጅ በትግበራ ሂደት የታዩ ክፍተቶችን በተለይም የመንግስት ሠራተኞች አስተዳደርን ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽነት እና ተጠያቂነት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት፤ እንዲሁም ከጊዜው ጋር የሚራመድ የአስራር ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ በሀገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ እና የቀጠሉ ተደራራቢ እና ሰፊ የተጎጂና የአጥፊ ወሰን ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ አሰራሮች በእውነት፣ በዕርቅ፣ በምህረት እና በፍትሕ ላይ የተዋቀረ እና በግልፅ ፖሊሲ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን አካታች፣ ሰብአዊ መብት ተኮር በሆነ እና በተሰናሰለ መንገድ ባለመተግበራቸው የሚፈለገውን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም። ስለሆነም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በተደራጀ፣ በተቀናጀ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመምራትና ለመተግበር እንዲቻል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.