Fana: At a Speed of Life!

የሳተላይት መረጃዎችን በመጠቀም የምርምር ሥራዎች እየተሰሩ ነው – ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳተላይት መረጃዎችን ለተቋማት ተደራሽ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እንዲጎለብቱ እየተሰራ መሆኑን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በጂኦ-ስፓሻል ዘርፍ መረጃ ለተቋማት ተደራሽ ማድረግ በሚያስችለው ሁኔታዎች ላይ ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቤተልሔም ንጉሴ (ኢ/ር)÷ ኢንስቲትዩቱ ለአምስት ዓመታት የሳተላይት መረጃዎችን ለማግኘት ከቻይና የተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ጋር ሥምምነት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህንም ተከትሎም አሁን ላይ የሦስት ሳተላይቶች መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ወደ መረጃ ቋት እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ኢንስቲትዩቱ እነዚህን መረጃዎች በመጠቀም የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለሌሎች ተቋማት የሳተላይት መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እንዲጎለብቱና የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ በትኩረት እየሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የሪሞት ሴንሲንግ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ብርሃን ገሠሠ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የሳተላይት መረጃዎችን ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና ተያያዥ ሥራዎች መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል።

ለአብነትም የሰብል ምርትን ለማሳደግ፣ የእንስሳት ልማትን ለማጠናከርና የተፈጥሮ አደጋዎችን የመከላከል ተግባራትን ለማከናወን የሳተላይት መረጃዎች ወሳኝ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

በመሆኑም ተቋማት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ሥምምነት በመፈጸም የሳተላይት መረጃዎች ማግኘት እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.