Fana: At a Speed of Life!

የፀጥታው ምክር ቤት በፍልስጤም የተመድ አባልነት ጥያቄ ላይ ድምፅ ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በፍልስጤም የአባልነት ጥያቄ ላይ በነገው እለት ድምፅ እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡

ከምክር ቤቱ 15 አባል ሀገራት ዘጠኙ ድምጽ የሚሰጡ ከሆነ እና ከአምስቱ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው ሀገራት የተቃውሞ ድምፅ ከሌለ የፍልስጤም የተመድ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ያገኛል ተብሏል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት የፍልስጤም የአባልነት ጥያቄ በ13 የምክር ቤቱ አባላት ተቀባይነት እንዳገኘ የተገለፀ ሲሆን የእስራኤል ወዳጅ የሆነችው አሜሪካ ግን ጉዳዩን አለመቀበሏ ነው የተገለፀው፡፡

ፍልስጤም የተመድ አባል የምትሆን ከሆነ ሙሉ የሀገርነት እውቅና የምታገኝ ቢሆንም ነገር ግን የውሳኔ ሃሳቡን አሜሪካ አለመቀበሏ የአባልነት ጥያቄዋን ሊያሳጣት እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

አሜሪካ በበኩሏ የፍልስጤምን ነፃ ሀገርነት እውቅና ለመስጠት ከተመድ ይልቅ በእስራኤል እና በፍልስጤም በኩል ቀጥተኛ ድርድር መደረግ አለበት ስትል ገልፃለች፡፡

ፍልስጤምን የነፃ ሀገርነት ጥያቄን ለመመለስ በፈረንጆቹ 1990 በእስራኤል እና በፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርጅት መካከል ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም ከግዛት ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፍልስጤም ነፃ ሀገር ሳትሆን መቆየቷን አሽራቅ አል አዋሳት ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.