Fana: At a Speed of Life!

የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የብሪክስ አባል ሀገራት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቴክኖሎጂ እድገትን ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የብሪክስ አባል ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።

10ኛው የብሪክስ የ“ወርኪንግ ግሩፕ” ስብሰባ ሁሉም የብሪስክስ አባል ሀገራት የዘርፉ ሃላፊዎች በተገኙበት ከሚያዝያ 16 እስከ 17 በሩሲያ ሞስኮ ተካሂዷል፡፡

በጉባኤዉ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የተመራ ልዑክ ተሳትፏል፡፡

በመድረኩ ወ/ሮ ትዕግስት÷ በአሁኑ ወቅት የብሪክስ አባል ሀገራትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የዓለም ሃገራት የሳይበር ደህንነትን ዋና ጉዳያቸው እንዳደረጉ ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን ደህንነት ጉዳይ በቀጣይም የብሪክስ አባል ሀገራትም ወሳኝ የውይይት አጀንዳ ሆኖ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

አባላቱ የሳይበር ጥቃት ስጋቶችን የመቋቋም አቅምን በማጠናከር ደህንነቱ የተጠበቀ ዓለም አቀፋዊ ዲጂታል አካባቢን መፍጠር እንዳለባቸውም መግለጻቸውን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ አባል ሀገራቱ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ደህንነት፣ የመረጃ ልውውጥ፣ የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም የተሻሉ ልምዶችን ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።

ወ/ሮ ትዕግስት ከመድረኩ ጎን ለጎን ከተለያዩ የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የሁለትዮሽ ውይይቶችን እንዳደረጉም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.