Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በትኩረት እየሰራ ነው – አቶ ዑሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዑሞድ ኡጁሉ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከአኝዋሃ ዞን ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ዛሬ በጎግ ወረዳ በመከሩበት ወቅት ነው።

የክልሉ መንግስት የህዝቡን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በዘላቂነት ሰላም ለማስፈን መንግስት ለሚያደርገው ጥረት የማህበረሰቡ እገዛና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው አቶ ዑሞድ የተናገሩት፡፡

የህዝቡን ህይወት እንዲቀይሩ ታቅደው የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማሳካት በዋናነት በየአካባቢው የተረጋጋ ሰላም ማስፈን አስፈላጊ መሆኑንም ገልፀዋል።

በህዝቦች መካከል ያለውን ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር እሴቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማፅናት ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሳካት የህዝቡ ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ናቸው።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ሰፍኖ የቆየውን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ አካላትን በህግ ለመጠየቅ መንግስት እያደረገ ላለው ጥረት ህዝቡ ተባባሪነቱን ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት አሁን ላይ የጀመራቸውና ማህበረሰቡን ያሳተፉ የሰላም ግንባታ ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የአመራር አባላትን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተዋቂ ግለሰቦች እና የህብረተሰቡ ተወካዮች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.