Fana: At a Speed of Life!

አቶ አረጋ ከበደ የክልሉን ዘመናዊ የመንገድ ሥራዎች አፈጻጸም ተመለከቱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ እና ሌሎች የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በባሕር ዳር ከተማ የሚገነቡትን የዘመናዊ የመንገድ ሥራዎች አፈጻጸም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከልደታ በማርዳ እብነ በረድ ፋብሪካ አቋርጦ ወደ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚዘልቀው ዘመናዊ የአስፋልት መንገድ ግንባታ የምልከታቸው ትኩረት ነበር።

ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ መንገዶቹ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ አሥፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ይደረጋል ።

የክልሉ ም/ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በበኩላቸው ÷የምልከታው ዋና ዓላማ እየተሠራ ያለው ዘመናዊ መንገድ ደረጃውን ጠብቆ እና ከተሰጠው ጊዜም በፈጠነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ነው ብለዋል።

መንገዱ ከሚገነባበት ቦታ እና ከሚያስተሳስራቸው ቀበሌዎች አንጻር ሲታይ የባሕርዳርን የወደፊት እድገት ታሳቢ ያድረገ ነውም ብለዋል።

መንገዱ ከመኪና መተላለፊያነት በተጨማሪ ደረጃውን የጠበቀ የእግረኛ፣ ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራት እና የብስክሌተኛ መተላለፊያን ጨምሮ የሚገነባ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

መንገዱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በፈጠነና ጥራቱን በጠበቀ የግንባታ ሂደት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ተከስቶ የቆየው የሰላም ችግር በርካታ ፕሮጀክቶችን የፈተነ ቢሆንም ይህ የመንገድ ግንባታ ግን በችግሮች ውስጥም ሆኖ በጠንካራ አፈጻጸም ውስጥ እያለፈ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

አቶ አበዱ አክለውም ፥ ከተቀመጠለት ጊዜ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የመጠናቀቅ እድል እንዳለውም ገልጸዋል።
የመንገዱ ግንባታ የፋይናንስ ችግር እንደገጠመው የተገለጸ ሲሆን ፥ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስፋልት የማንጠፍ ሥራ እንደሚከናወንም መገለጹን የዘገበው አሚኮ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.