Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ500 ሚሊየን ብር የተገነባ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በ500 ሚሊየን ብር የተገነባው የዮ ሆልዲንግ ዘመናዊ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ኩባንያ ምርት ማምረት ጀምሯል።

ኩባንያው የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ለክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላትና እና ለባለድርሻ አካላት ዛሬ በአሶሳ የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ታደሰ በወቅቱ÷በ500 ሚሊየን ብር በካማሽ ዞን ምዥጋ ወረዳ የተገነባው የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

የድንጋይ ከሰል ማምረቻው በዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን በላይ ጥሬ ድንጋይ ከሰል የማቀነባበር አቅም እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

አስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴም 77 ሺህ 500 ቶን የከሰል ድንጋይ ምርት በማቀነባበር ለሀገር ውስጥ የሲሚንቶ፣ ብረታ ብረት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ወረቀት፣ ሴራሚክ እና ሌሎች ፋብሪካዎች ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

ፋብሪካው የማቀነባበር ሥራውን በሙሉ አቅሙ ለመቀጠል እንዲችል መንግስት ሰላምን ከማስቀጠል ባሻገር መብራት፣ መንገድና መሠረተ ልማቶችን በማጠናከር ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የቤንሻንገል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቃሲም ኢብራሂም በበኩላቸው÷ የኩባንያው እንቅስቃሴ ለሌሎች ባለሃብቶች እና ኩባንያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኩባንያው በከሰል ማምረት ሂደት የአካባቢ ጥበቃ ህጎችን በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባውም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመድረኩ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.