Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብና ቤት ቆጠራን አራዘመ፤ አዲስ አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤም መረጠ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን የጀመረው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ አራዘመ።
 
ምክር ቤቱ በስብሰባው ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የተራዘመው የህዝብና ቤት ቆጠራ አሁንም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለህዝብ ጤናና ደህንነት ሲባል እንዲራዘም ወስኗል።
 
የሚመለከታቸው አካላት የቫይረሱን ስርጭትና ጉዳት ገምግመው መቀነሱን ወይንም ጉዳት ማድረሱ ማቆሙን ማረጋገጥ ሲችሉ ቆጠራው በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲካሄድ ወስኗል።
 
ምክር ቤቱ ከሰዓት በኋላ የተመለከተው ሌላው ጉዳይ በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉትን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ነው።
 
በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የዞን ምክር ቤቶች የቀረቡ የክልልነት ጥያቄዎችን ምላሽ ለማሰጠት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው የመነሻ ምክረ ሃሳብ በሌሎች ሃሳቦች ዳብሮ የመጨረሻ ውሳኔ በራሱ በኮሚቴው እንዲሰጥበት ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል።
 
የከፋ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የከምባታ ጠምባሮ፣ የሃዲያ፣ የጋሞ፣ የጉራጌ፣ የጌዴኦ፣ የጎፋና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ማቅረባቸውን ኮሚቴው ገልጿል።
 
በመሆኑም የክልልነት ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ የጋራ መድረኮችን የማመቻቸት፣ የምክር ቤቱን አስፈጻሚ ከክልሎች አስፈጻሚዎች ጋር የማገናኘትና የማወያየት፣ ከዚህ ቀደም የተጠኑ ጥናቶችንና የሰላም አምባሳደሮችን ስራ እንዲሁም ህዝብን በማወያየት የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ ቋሚ ኮሚቴው ይዞ እንዲቀርብ በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ተወስኗል።
 
ምክር ቤቱ በመጨረሻ በቅርቡ በፈቃዳቸው ስልጣን በለቀቁት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ምትክ አቶ አደም ፋራን አፈጉባኤ አድርጎ መርጧል።
 
ቀደም ሲል የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ የነበሩት አቶ መሐመድ ረሽድ ዛሬ በአፈጉባኤነት ከተመረጡት ጋር ከአንድ ክልል የተወከልን በመሆኑ ለሌሎች እድል መስጠት ይግባል በሚል በፈቃዳቸው ሀላፊነታቸውን ለቀዋል።
 
ያንንም ተከትሎ በምትካቸው ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በምክትል አፈጉባኤነት ተመርጠዋል።
 
በተስፋዬ ከበደ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.