Fana: At a Speed of Life!

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራው ልዑክ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራው ልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ልዑኩ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱን፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስታሊና ጂኦርጄቫ፣ ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የምስራቅ እና የደቡባዊ አፍሪካ ሃላፊ ቪክቶሪያ ክዋክዋ፣ ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአይዳ ሃላፊ አኪህኮ ኒሺዮ እና ከሌሎች የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር መክሯል፡፡

በምክክሩ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ስለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታና የወደፊት ተስፋ፣ የተረጋጋ ሀገራዊ ጥቅል ኢኮኖሚ ለማምጣት እየተሰራ ስላለው የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትና የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርታማነትን ማሳደግ እና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ይገኙበታል፡፡

ተቋማቱ ኢትዮጵያ እየወሰደቻቸው ያሉትን ወሳኝ እርምጃዎች ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እና የዋጋ ንረትን ለመቅረፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለተኛ ምዕራፍ ሀገር አቀፍ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አድንቀዋል።

በተጨማሪም ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን በሙሉ አቅም ለመተግበር ከማስቻል አኳያ በቀጣይ መደገፍ እና አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.