Fana: At a Speed of Life!

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ለተሽከርካሪ መገጣጠሚያና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ እና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጡ።

ከተመሰረተ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረው የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ለሀገርና ለተቋሙ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢንዱስትሪው በአዲስ መልኩ ከተደራጀ በኋላ በተሰሩት ስራዎች ከኪሳራ ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩን አመላክተዋል፡፡

ተቋሙ የራሱን ገቢ በማመንጨት ለሰራዊቱ መሰረታዊ ጥቅም ለማሟላት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ስለመሆኑ መናገራቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሰራዊቱን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በማዕድንና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ለመስራት የተቀመጠው አቅጣጫ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ኃይለማርያም የመከላከያ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ እና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ከሽርሽር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመሆን የሚገነባው መሆኑን ተናግረዋል።

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት ኢንዱስትሪው፤ በ30 ሄክታር ላይ የሚያርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ያሟሉ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ከመገጣጠምና ከማምረት ባለፈ በቀጣይ ፕሮጀክቱን የማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸውም ነው ያስረዱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.