Fana: At a Speed of Life!

ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የግብር ጉዳት በማድረስ ተደራራቢ ክስ የቀረበበት ግለሰብ በ4 ክሶች ነጻ ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የግብር ጉዳት አድርሷል ተብሎ ተደራራቢ ክስ የቀረበበትን ግለሰብ በአራት ክሶች ነጻ በማለት በሁለት ክስ ብቻ እንዲከላከል ብይን ተሰጠ።

የዐቃቤ ሕግ የምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ብይን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በረከት አለልኝ በተባለ ተከሳሽ ላይ በነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም በሀሰተኛ ሰነድ የባንክ ሒሳብ መክፈት፣ በህገወጥ መንገድ ንግድ ፍቃድ ማውጣትና ማደስ፣ የታክስ አዋጁን መተላለፍ፣ ሀሰተኛ ሰነዶችን መጠቀም፣ የገቢ ደረሰኞችን አትሞ ለተለያዩ ነጋዴዎች ማሰራጨት የሚል ተደራራቢ ሰባት ክሶች በዝርዝር ማቅረቡ ይታወሳል።

በተለይም በመስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም እና በመስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም ፍቃድ በማሳደስ የተመዘገበዉ በአስመጪነት ንግድ ስራ ዘርፍ ሆኖ ሳለ ምንም አይነት እቃ ከዉጭ ሀገር ሳያስገባ እና የሀገር ውስጥ የዕቃ ግዥ ሳይፈጽም ከወሰደው የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ደረሰኞችን በማተም ለ339 ግብር ከፋዮች 1 ሺህ 663 ደረሰኞችን በማሰራጨት በ15 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ 25 ቢሊየን 989 ሚሊየን 943 ሺህ 223 ብር ከ83 ሳንቲም ጉዳት ደርሷል በማለት ዐቃቤ ሕግ ካቀረባቸው ክሶች መካከል ጠቅሶ ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ 30 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል በማለት ያቀረበው ዝርዝር ክስ ለተከሳሽ ከደረሰው በኋላ ግለሰቡ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግ የኦዲት ባለሙያዎችን ጨምሮ 13 የሰው ምስክሮችን እና 23 ገላጭና አስረጂ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የተሰሙ የሰው ምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት ብይን ሰጥቷል።

በዚህም በ1ኛና በ2ኛ ክሶች ላይ ማለትም ሰለሞን ሙሉ ከውን በሚል የፈጠራ ስም በወጣ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያና ሀሰተኛ ውክልና መሰረት የንግድ ፍቃድ በማውጣትና በማሳደስ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ተብሎ የቀረበውን ክስ በሚመለከት፤ ንግድ ፍቃድ መውጣቱንና መታደሱን እንጂ ሰለሞን ሙሉ ከውን በተባለው ሰው ወይም በተወካይ ንግድ ቢሮ ቀርቦ ንግድ ፍቃዱን ማን አወጣ ማን አሳደሰ የሚለው አሳማኝ ማረጋገጫ ያልቀረበ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አብራርቷል።

በተጨማሪም ከምስክሮች ቃል አሰጣጥ አንጻር በሰነዶች ማረጋጋጫ ተቋም አንድ ሰው በአካል ሳይቀርብ የጣት አሻራ ሳይሰጥና ሳይፈርም ውክልና እንደማይሰጥ መረዳቱን በመጥቀስ ሰለሞን ሙሉ ከውን በሚባል ሰው አሻራ ሰጥቶ ፈርሞ፣ በአካል ቀርቦ ውክልና የሰጠና ንግድ ፍቃድም ያወጣና ያሳደሰ መሆኑን ግምት መያዙን በማብራራት ከ1ኛ እና ከ2ኛ ክስ ነጻ ብሎታል።

3ኛ እና 4ኛ ክስን በሚመለከት በ2010 እና በ2011 ዓ.ም ከውጭ ሀገር ዕቃ ሳያስገባና ምንም አይነት ሽያጭ ሳያከናውን ሀሰተኛ የተጭበረበሩ ሰነዶችን የአመታዊ የግብር ሪፖርትን ለግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ማስገባቱ መረጋገጡን በመጥቀስ 3ኛ ክስ ከ4ኛ ክስ ጋር ተጠቃሎ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ለ339 ግብር ከፋዮች 1 ሺህ 663 የገቢ ደረሰኞችን አትሞ በማሰራጨት የንግድ ትርፍ እና የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በ15 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ 25 ቢሊየን 989 ሚሊዮን 943 ሺህ 223 ብር ከ83 ሳንቲም ጉዳት መድረሱን በማስረጃ መረጋገጡን ገልጾ፤ 5ኛ ክስን ተከሳሹ እንዲከላከል በሙሉ ድምጽ ብይን ተሰጥቷል።

በ6ኛ ክስ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በተከራየው ሱቅ ውስጥ ህገወጥ እውቅና የሌለው የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያና ኮምፒውተሮች በገቢዎች ሰራተኞች ተገኝቷል ተብሎ የቀረበው ክስን በሚመለከት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያው ከጁፒተር ንግድ ስራዎች ድርጅት የተገዛና የተገጠመ መሆኑን መረጋገጡን ችሎቱ ጠቅሶ፤ እውቅና የሌለው ህገወጥ መሳሪያ ተገኝቷል በሚል የቀረበውን ክስ በሚመለከት ግን ማስረጃ አለመቅረቡን ገልጾ ተከሳሹን ነጻ ነው ብሎታል።

7ኛ ክስን በሚመለከት የታክስ አስተዳደር አዋጅን በመተላለፍ ግብይት ሳይኖር ህገወጥ ደረሰኝ መጠቀም የሚለው ክስ ከ5ኛ ክስ ዝርዝር ጋር በተመሳሳይ በሀሳብ መደራረብ ያለው መሆኑን ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ በዚሁ 7ኛ ክስ ተከሳሹን ነጻ በማለት ብይን ሰጥቷል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የመከላከያ ማስረጃ እንዳለውና እንደሌለው ለማረጋገጥ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም በተከሳሽ ጠበቃ በኩል ግን ከመከላከያ በፊት ተከሳሹ ይከላከል በተባለባቸው ክሶች ላይ የቀረበው ድንጋጌ ዋስትና የማያስከለክል ድንጋጌ መሆኑን ጠቅሶ ዋስትና እንዲፈቀድ ተጠይቋል።

ዐቃቤ ሕግ በዋስትናው ላይ አስተያየቱን በጽሁፍ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ መነሻ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን መልስ ለመጠባበቅ ለፊታችን ሰኞ ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.