Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ለሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት ይሰራል- አቶ ተስፋዬ በልጅጌ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተግባራዊነትና ውጤታማነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት አመራሮችና ሌሎች በተገኙበት በሽግግር ፍትህ ፖሊሲና የፌደራል የአስተዳደር ስነ-ስርአት አዋጅ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዳነሱት፤ በኢትዮጵያ በቀደሙ ስርዓቶች የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በታሪክ ምክንያት የሚነሱ አለመግባባቶች፣ የዴሞክራሲ ስርዓት አለመጎልበት፣ ለዘመናት የተከማቹ የፖለቲካ ቀውሶች አሉ።

ለእነዚህ ችግሮች እልባት ከመስጠት አኳያ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሚመጋገብና ሂደቱን የሚያሳልጥ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

መንግስት ፖሊሲው እንዲዘጋጅ ከማድረግ ጀምሮ ቁርጠኛ የፖለቲካ አቋም መውሰዱን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ለረዥም ጊዜ ስር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት ከችግር መውጫ አንዱ መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትናንት ቁርሾዎችን በእርቀ ሰላምና ይቅርታ በመዝጋት ለነገ ትውልድ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ማስተላለፍ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፤ ትውልዱ ችግሮችን ቀርፎ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር ኃላፊነት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

ሀገራዊ የሆኑ ችግሮች በይደር የሚታለፉ ባለመሆናቸው በአንድነት ለመፍታት አሁኑኑ መነሳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ገለልተኛ ተቋማትን በማደራጀት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ለፖሊሲው ተፈጻሚነትም አስቻይ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም አንስተዋል።

በሌላ በኩል የፌደራል የአስተዳደር ስነ-ስርአት አዋጅ የተጀመረው የለውጥ ስራ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሚናው የጎላ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አዋጁ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የተቋማት ኃላፊዎችና ሙያተኞች ተግባራዊነቱ ላይ በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.