Fana: At a Speed of Life!

ኤምባሲው በፓኪስታን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፓኪስታኑ የዘላቂ ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን አስጀመረ፡፡

 

ኤምባሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው÷በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ይፋ የተደረገው በኢስላማባድ በተካሄደው የኢትዮ-ፓኪስታን ወዳጅነት ሴሚናር ላይ ነው፡፡

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በዚህ ወቅት ÷የአረንጓዴ ልማት የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር እንዲታረቅ እንዲሁም ለማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ያስገነዘቡት አምባሳደሩ÷የኢትዮጵያ መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ በማድረግ በ2050 ከካርበን ነጻ ግብን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፓኪስታን መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያሳየውን ተነሳሽነት አድንቀው ጥረቱ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

የፓኪስታን የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጥበቃ አስተባባሪ ሮሚና ኩርሺድ አላም በበኩላቸው÷በአረንጓዴ ልማት ኢኒሼቲቭ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መስሪያ ቤታቸው አለም አቀፍ አረንጓዴ ፓርላሜንታሪ ኮከስ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቆሙት አስተባሪው ÷ኢትዮጵያ እቅዱ እንዲሳካ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.