Fana: At a Speed of Life!

በሚቀጥሉት10 ቀናት የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት10 ቀናት የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎች በጠተናከረ ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በተለይም የምድር ወገብን አቋርጦ ወደ ሀገራችን የሚገባው እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተሻለ የደመናና የዝናብ ሥርጭት በደቡባዊው አጋማሽ፣ በመካከለኛውና በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ፤ በደቡብ ምስራቅ፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ፣ በመካከለኛው፣ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

በመሆኑም የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ ምስራቅ፣ መካከለኛው፤በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቅጸበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፤ ቦረና፤ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፤ አዲስ አበባ፤ ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የአፋር ክልል ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፤ የምስራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የሱማሌ ክልል ዞኖች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፤ በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፤ ከአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የዋግኸምራ ዞኖች፣ የጋምቤላ ክልል ዞኖች፤ ከቤንሻንጉል ክልል የአሶሳ፣ የማአኮሞ ልዩ ወረዳ፤ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል በአፋር ክልል፣ ሀረር፣ድሬዳዋ፣ምስራቅ ሸዋ፣ የሶማሌ ክልል ዞኖች፣ አዲስ አበባ እና በምስራቅ አማራ አካባቢዎች ከሚኖረው ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በመነሳት ቅጸበታዊ ጎርፍ የሚስከተል አቅም ስለሚኖረው ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.