Fana: At a Speed of Life!

የሌማት ትሩፋት የኢትዮጵያን መልክ ከሚቀይሩት የዚህ ትውልድ ዓድዋዎች አንዱ ነው – ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሌማት ትሩፋት የኢትዮጵያን መልክ ከሚቀይሩት የዚህ ትውልድ ዓድዋዎች አንዱ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ሀገራዊው የሌማት ትሩፋት ሥራዎች የአንድ ዓመት ተኩል አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በሃዋሳ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና የግብርና ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው እንዳሉት ፥ የሌማት ትሩፋት የኢትዮጵያን መልክ ከሚቀይሩት የዚህ ትውልድ ዓድዋዎች አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ትልቁ አብዮት በሬን ከቀንበር ነጻ በማውጣት የሚከናወን ነው ይባላል ፤ ይህም ማለት ግብርናችን መዋቅራዊ ሽግግር ሲያደርግ የሚሳካ ነው እንደ ማለት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አክለውም ግብርናችን መዋቅራዊ ሽግግርን ሲያደርግ ድህነት ይቀንሳል፤ በምግብና በሥነ ምግብ ራሳችንን እንችላለን፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፤ የውጭ ንግድ ገቢያችን ያድጋል፤ ከውጭ የሚገቡት የግብርና ምርቶች በሀገር ምርት ይተካሉም ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ይሄንን ታላቅ አብዮት ለማሳካት ባለፉት ዓመታት ብርቱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡

ግብርናው ወደ ዘመናዊነት ተሸጋግሮ በሬን ከቀንበሩ ማላቀቅ ገና አልቻለም ያሉት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ፥ ጥራቱን የጠበቀ እና በቂ የቴክኖሎጂ፣ የግብዓት አቅርቦትና ሥርጭት እጥረት እንዳለ በማንሳት በቁመናው ልክ የሚገባውን የፋይናንስ አቅርቦት አላገኘም ብለዋል።

የግሉ ባለሃብት ተሳትፎ አነስተኛ መሆንና የግብርና ምርምርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቱ ውጤታማ አለመሆኑን ገልጸው ፥ ይሄም ወገባችንን አሥረንና ክንዳችንን ሰብስበን የምንሠራው ታላቅ ሀገራዊ ሥራ ከፊታችን መኖሩን ያሳያል ነው ያሉት፡፡

ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ የለውጡ ትሩፋት ከጎበኛቸው ዘርፎች አንዱ ግብርና መሆኑን ጠቅሰው÷መንግሥት ለግብርናው ዘርፉ የተለየ ትኩረት መስጠቱንና የምግብ ሉዓላዊነታችንን ማስከበርን አላማ አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንሥቶ በአርሶ እና አርብቶ አደሩ ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት እና መነሣሣት ለመፍጠር መቻሉንም ነው ያነሱት፡፡

የሌማት ትሩፋትን በሚፈለገው መጠንና ጥራት አከናውኖ የሚታሰበውን ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ፣ የሙያተኞች እገዛ፣ የከፍተኛ አመራሩ የቅርብ ክትትል፣ ድጋፍ እና ቁርጠኛ አመራር መስጠት ወሳኝ ነውም ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የአንድ ዓመት ተኩል የሌማት ትሩፋት አፈጻጸም እና የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከት ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በአንድ ዓመት ተኩል አፈጻጸም ከእቅድ በላይ መሆኑን ጠቁመው ፥ ካለው ሃብትና አቅም አንጻር ብዙ ሥራ ይጠይቃል ነው ያሉት።

እንደሀገር ያለው አፈጻጸም ከቦታ ቦታ የሚለያይ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ፥ የግምገማ መድረኩ ይህንና የሚስተዋሉ ሌሎች ክፍተቶችን በማስተካከል በአዲስ ንቅናቄ ሥራውን ለመተግበር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በፍሬህይዎት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.