Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራ ነው – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገሪቷን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን በራስ አቅም ለመፍታት የሚያስችላት ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም (ዶ/ር)÷ በሀገሪቷ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ ባሳለፍነው የካቲት ወር በሚኒስትሮች ም/ቤት መጽደቁን አስታውሰዋል።

ፖሊሲው በዋናነት የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን በራስ አቅም በመፍታት የተረጂዎችን ቁጥር መቀነስና በምግብና ስነ ምግብ እጥረት የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የተረጂዎችን ቁጥር በመቀነስ ሂደትም የመረዳዳት ባህልንና ምርታማነትን ማሳደግ ቀዳሚ ሲሆን÷ በተለይም በምግብና ስነ-ምግብ እጥረት ተጎጂ የሆኑ ህጻናትና እናቶችን ትኩረት ያደረገ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በሀገሪቷ ከ1 ሚሊየን የሚበልጡ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትና ከ4 ሚሊየን የሚበልጡ የማህበረሰብ ክፍሎች በምግብና ስነ ምግብ እጥረት ጉድለት ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ ብለዋል።

በመሆኑም በየአካባቢው ባሉ ሀገር በቀል የሰብዓዊ ድጋፍ ልምዶችና ተሞክሮዎችን በማስፋትና በማጠናከር የተረጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በምግብና ስነምግብ ላይ የሚሰራው ስራ በአካልና በአዕምሮ ያደጉ ህጻናት በመፍጠር በትውልድ ግንባታ ላይ የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለዚህ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ቤተሰብ ለተረጂነት ሲጋለጥና ችግር ላይ ሲወድቅ የረጂ ድርጅቶችን ከመጠበቅ ይልቅ በቆየ ኢትዮጵያዊ ልምድ በአካባቢና ቀበሌ ደረጃ የመረዳዳት ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ በየአካባቢ ያሉ የመደጋገፍ ልምዶችን በተደራጀ መንገድ ለመምራት የሚያስችል እቅድ ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የችግሩን አሳሳቢነት መረዳት፣ በየአካባቢው ያሉ ልምዶችን መፈተሽ፣ ልምዶቹን ማደራጀትና ቅርጽ በማስያዝ ለትግበራ አስቻይ የሆነውን የፖሊሲ ድጋፍ ተዘጋጅቶ ምላሽ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል።

ከምክክር መድረኮች ከሚገኙ ልምዶችና ከተቀመጡ አቅጣዎጫች መነሻ ክልሎችም የራሳቸውን ፕሮግራም ነድፈው ለትግበራው በትጋት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.