Fana: At a Speed of Life!

የናይል ተፋሰስ ሀገራት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍትሃዊ አጠቃቀም የትብብር ማዕቀፍን እንዲፈርሙ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይል ተፋሰስ ሀገራት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዘላቂና ፍትሃዊ የአጠቃቀም ስርዓትን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት የትብብር ማዕቀፉን ሊፈርሙና ሊያጸድቁ እንደሚገባ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ጥሪ አቀረበ፡፡

የናይል ተፋስስ ኢኒሼቲቭ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ኢኒሼቲቩ የተፋሰሱን ፀጋዎች በጋራ በማልማት ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አላማ አድርጎ እየሰራ ነው፡፡

25 ዓመታትን ያስቆጠረው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በትብብር ማልማት፣ የውሃ ሃብት ስራ አመራር እና የውሃ ሃብቶች ልማት ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

ኢኒሼቲቩ ባለፉት ዓመታት ባደረጋቸው ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞች በሃይል ትስስር በውሃ ሃብት ስራ አመራር በአቅም ግንባታ እና የህዝብ ኑሮ የሚያሻሽሉ ውሃ ነክ ኢንቨስትመንቶችን ገቢራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።

በሰላምና ደህንነት፣ በውሃ ዋስትና፣ በኃይል፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በምግብ ዋስትና መሰል ፈተናዎችን ለመሻገር እንደ ሀገርና እንደ ተፋሰስ በትብብር መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭን ወደ ናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ቀጣናዊ ተቋም ለማሸጋገርና በተፋሰሱ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዘላቂና ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን ለመምራት በፈረንጆቹ 2010 የተደረሰውን የትብብር ማዕቀፍ ያልፈረሙ አባል ሀገራት እንዲፈርሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ አብርሃም አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ኢኒሼቲቩ በፈተናዎች ውስጥም ሆኖ ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እየተሳሰረች መሆኑን ገልጸው÷በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊና የጋራ ተጠቃሚነት ዕውን እንዲሆን አበክራ እንደምትሰራ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴዔታው÷ እስካሁን ግን መደላድል ቢፈጠርም ባላት ውሃ ሃብት ልክ ተጠቃሚ አይደለችም ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.