Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ 476 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ለዝርዝር እይታ መራ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
 
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ በተካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስት የ2013 ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቷል።
 
የ2013 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት 476 ቢሊየን 12 ሚሊየን 952 ሺህ 445 ብር እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል።
 
በዚህም በ2013 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች ብር 133 ቢሊየን 321 ሚሊየን 561 ሺህ፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 160 ቢሊየን 329 ሚሊየን 788 ሺህ፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 176 ቢሊየን 361 ሚሊየን 602 ሺህ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 6 ቢሊየን በጠቅላላ ብር ነው የተያዘው።
 
የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የፌዴራል መንግስት የ2013 ረቂቅ በጀት በተመለከተ ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
አቶ አህመድ ሺዴ በማብራሪያቸውም፦ የ2013 በጀት ግብዓትን ከውጤት ጋር የሚያዛምድ እንዲሁም ኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
 
በ2013 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ8 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ የገንዘብ ሚነስትሩ አቶ አህመድ አክለው ተናግረዋል።
 
የማክሮ ኢኮኖሚው ከገጠመው ተግዳሮት እንዲላቀቅ መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።
 
በዚህ ወቅትም ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ ተቀዛቅዞ የነበረው ኢኮኖሚ እያንሰራራ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።
 
ምክር ቤቱ በቀረበለት የ2013 ረቂቅ በጀት ላይ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስቶ ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠበት በኋላ ለዝርዝር እይታ ለገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
 
ምክር ቤቱ በመቀጠልም የገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል ስለማዛወር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።
 
የልማት ድርጅቶችን ወደግል ስለማዛወር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በዝርዝር ከተወያየበት በኋላ አዋጁን በ16ተቃውሞ፣ በ3 ድምጸ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.