Fana: At a Speed of Life!

የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም የማሳደጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በብቃት ለመምራት የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልገሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለፌዴራል እና ለክልል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ሲሰጠው የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቅቋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ስልጠናው በአምስት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

የመጀመሪያው በአስተሳሳሪ ትርክት ግንባታ ምንነት፣ የሚካሄድባቸው አቅጣጫዎች ቴክኒኮች እና ስልቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን ሁለተኛው ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰላም ግንባታ ሥራዎች እንዲሁም የአስር ዓመቱ የመንግስት የልማት እቅድን ማእከል አድርጎ የተዘጋጀው የሶስት ዓመት የመካከለኛ ዘመን የልማት መርሐ ግብርም የስልጠናው ትኩረት ነበር ብለዋል።

የህዝብ ግንኙነት መሰረታዊ ሃሳቦች እና መሳሪያዎች ትግበራ ሌላኛው ስልጠናው ያተኮረባቸው ርእሰ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ስልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎች ሀገራዊ ተልዕኮዎችን እና የመንግስት ዋና ዋና ትኩረቶች እንዲገነዘቡ እንዲሁም በእውቀት እና በክህሎት የተሟላ አቅም እንዲፈጥሩ ያስቻለ መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣይም በየደረጃው ያለውን ሀገራዊ የመረጃ ፍሰት ለማቀናጀት የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ በርካታ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፥ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ለስራው መሳለጥ የሚረዱ አሰራሮች እና መመሪያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን እና ሲጠናቀቁ ለዘርፉ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.