Fana: At a Speed of Life!

ታይዋን በድጋሚ በተከታታይ ከባድ ርዕደ መሬት ተመታች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታይዋን 17 ሰዎችን ለህልፈት ከዳረገው ርዕደ መሬት አደጋ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ከትናንት ምሽት እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ በድጋሚ ለሰዓታት ከባድ በሆነ ተከታታይ ርዕደ መሬት መመታቷ ተገልጿል፡፡

በመጀመሪያ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 5 ሆኖ የተመዘገበ ሰኞ ምሽት በደሴቲቱ ምስራቃዊ ሁዋሊን ግዛት የደረሰውን ርዕደ መሬት ተከትሎ አነስተኛ መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተመላክቷል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 0 እንዲሁም 6 ነጥብ 3 ሆነው የተመዘገቡ የርዕደ መሬት አደጋዎች መከሰታቸውን የደሴቲቱ የአየር ሁኔታ አስተዳደር የርዕደ መሬት ማዕከል አስታውቋል፡፡

በፈረንጆቹ ሚያዝያ 3 በደረሰው ርዕደ መሬት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ሕንፃዎችም ከዛሬ ጠዋቱ ክሰተት በኋላ በከፊል መውደቃቸውን የሁዋሊን ግዛት ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የማዕከላዊ የአየር ንብረት አስተዳደር የርዕደ መሬት ማዕከል በአደጋው የተጎዱ ሰዎች እንደሌሉና በሁዋሊን ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ትዕዛዝ እንደተላለፈ ማስታወቁን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡

ቀደም ሲል የደረሰው የርዕደ መሬት አደጋ በታይዋን ከ25 ዓመታት በፊት በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 7 ሆኖ ከተመዘገበውና 2 ሺህ 400 ሰዎችን ለህልፈት በመዳረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ህንፃዎችን ካወደመው ርዕደ መሬት በኋላ ከባዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.